Monday, December 29, 2014

ከማእበሉ መነሳት በፊት...


ተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኦሮሚያ ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለችም። የኦሮሚያ ወጣቶች ከግንቦት 2014 አመፅ የቀጠለ የመነሳሳት መንፈስ ላይ መሆናቸው ይሰማል። 5ኛውን የወያኔ የቁጩ “ብሄራዊ ምርጫ” ተከትሎ በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ የሚችለው አመፅ ወዴት እንደሚያመራ ካልታወቀ ውጤቱ አደገኛ ሊሆን ይችላል። 

ባለፈው ቅዳሜ በኦሜን (OMN) ቲቪ አንድ ልዩ ዝግጅት ቀርቦ ነበር። ዳባ ደበሌ ከኦሮሚያ አርቲስቶች ጋር አዳማ ላይ ባደረገው ቆይታ ድምፃውያን አሊ ቢራ እና ታደለ ገመቹ ሲናገሩ ተደምጠዋል። አሊ ቢራ እንዲህ አለ፣

“ኢትዮጵያ በሚሏት አገር ብዙ ጎጆዎች አሉ። ከጎጆዎቹ ሁሉ ትልቁ ጎጆ ኦሮሚያ ነው። ኦሮሚያን የከበቡት ትንንሽ ጎጆዎች ኦሮሚያ እንደነርሱ ትንሽ ጎጆ ይሆን ዘንድ ሊያፈርሱት ብዙ ሞከሩ። አልተሳካላቸውም። ስለዚህ በታላቁ ጎጆ ዙሪያ ከበው ኦሮሚያ ላይ መፀዳዳት ይዘዋል።”

አሊ ቢራ ከፍተኛ ጭብጨባ አስተናገደ። በመቀጠል ታደለ ገመቹ ተናገረ፣

“ቢፍቱ ኦሮሚያ የኪነት ቡድን 47 አባላት አላት። ከእነዚህ አባላት 27ቱ አማራዎች ሲሆኑ፣ ኦሮሞዎች 20 ብቻ ናቸው። የአኖሌ ሃውልት ምረቃ ሲደረግ በቢፍቱ ኦሮሚያ የተሰገሰጉ አማሮች የምኒልክ ምስል ያለበትን ቲሸርት ለብሰው፤ በላዩ ጃኬት ደርበውበት ወደ ሃውልት ምረቃው መጡ። ለመሆኑ የOPDO አመራር አባላት ይህን ታውቃላችሁ?”

እንደገና ሌላ ጭብጨባ...

በራሳቸው ድምፅና በራሳቸው ቋንቋ በሚነገረው፣ መስማት በሚፈልጉት አይነት ወግ ብቻ ተከበው የሚኖሩ ወገኖች እውነታውን ለመገንዘብ እድሉን አጥተዋል። ካሉበት ድረስ መጥቶ በቋንቋቸው የሚነግራቸውንም በፍርሃትና በጥላቻ ያስተናግዱታል። የጥንት አማራ ገበሬዎች ሲከፋቸው የሚያንጎራጉሯት አንዲት ውብ ዜማ ነበረች። እንዲህ የምትል፣

እንዲህ ጨሶ ጨሶ - የነደደ እንደሆን
የአመዱ መጣያ - ስርፋው ወዴት ይሆን?

ያለንበት ዘመን ከማእበሉ መነሳት በፊት ያለውን ፀጥታ ይመስላል። የሰሜን አበሻ ፖለቲከኞች እየተገላበጠ በመምጣት ላይ ያለውን ከባድ ማእበል ማስተዋልና አቋማቸውን መፈተሽ ካልቻሉ፤ ባልጠበቁት ጊዜና ወቅት ማእበሉ ጠርጓቸው ሊሄድ ይችላል። አሜሪካ ላይ ከተዋወቅሁዋቸው አብዛኛው ኦሮሞዎች አመለካከት መረዳት እንደቻልኩት የመጀመሪያው ጦርነት ወያኔን ማስወገድ ነው። ከወያኔ መወገድ በሁዋላ የሚከተለው ሁለተኛ ጦርነት የነፍጠኛው ሁዋላ ቀር አመለካከት መሆኑን ይናገራሉ።

በዳውድም ሆነ በሌንጮ፣ በቡልቻም ሆነ በመረራ ጉዲና የሚመሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚነሱ ጥያቄዎች ግባቸው ላይ ብዙ ልዩነት የላቸውም። የመገንጠልን አጀንዳ ለጊዜው ብናቆየው እንኳ፤ ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢያንስ የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ይጠይቃሉ። ሌላው ሁሉ ቢቀር የኦሮሞ ህዝብ አቅም በሌላቸው አሻንጉሊቶች መተዳደር አይፈልግም። በዚህ ጥያቄ ላይ ልዩነት ያለው ኦሮሞ ማግኘት በፍፁም አይቻልም።

እርጅና የተጫጫነው የህወሃት አመራርም ሆነ የኢትዮ አማራ ፖለቲከኞችበመጪው ዘመን የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ በትክክል ለመረዳት ካልሞከሩአደጋ ይገጥማቸዋል። እየተገላበጠ በዝግታ በመምጣት ላይ ያለው የኦሮሚያ የቁጣ ማእበል፣ በሙሉ ሃይሉ ከገነፈለ በሁዋላ ምናልባት ለማቆምና ለመቆጣጠር ጊዜና ችሎታ ላይኖር ይችላል። የማእበሉ የማዳረስ ችሎታም በኢትዮጵያ ሳይወሰን መላ አፍሪቃ ቀንድን ካለመረጋጋት ቀውስ ውስጥ ሊጨምራት ይችላል። የኦሮሚያ ጥያቄ አካባቢውን ሁሉ የማተራመስ ስፋትና ችሎታ ሊኖረው እንደሚችል ለመገንዘብ ቀላል ነው። በቅድሚያ አበሻ ፖለቲከኞች ከአባቶቻቸውከወረሱት የንቀት አባዜ መላቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ንቀት አእምሮን የሚጋርድ በሽታ ነው።

የቅዳሜማስታወሻ: Gadaa Ghebreab, January 1, 2015  Email:  ttgebreab@gmail.com

1 comment:

Anonymous said...

POST DATE: Monday, December 29, 2014
የኦሮሚያ ወጣቶች ከግንቦት 2014 አመፅ የቀጠለ ?? MAY 2014,

TYPICAL OF YOUR FICTITIOUS WRITING!