በሎስ አንጀሊስ ቆይታዬ ወደ ኤልያስ ወንድሙ ቢሮ ብቅ ብዬ ነበር። ብዙ አወራን። የታተሙ ዳሩ ግን ገና ወደ ገበያ ያልቀረቡ ዳጎስ ያሉ መጻህፍትን ሲያሳየኝ ልነጥቀው ምንም አልቀረኝ ነበር። ከነዚህ መጻህፍት አንዱ፣ አጤ ምኒልክን ይመለከታል። ሙዙንጉ ሲቀልድ “አፍሪቃ ላይ የሆን ነገር መደበቅ ስትፈልግ በመጽሃፍ ጻፈው” ይል ነበር። በሌላ አነጋገር አፍሪቃ ውስጥ የመጽሃፍ ሌባ የለም። ርግጥ አባባሉ የተጋነነ ነው። ከትርፍ አንጻር ኤልያስ ወንድሙ መጠጥ ቤት ወይም ቁርጥና ክትፎ ቤት ቢከፍት ያዋጣው ነበር።
ኤልያስ ምንም እንኩዋ አሳታሚነትን እንደ ቢዝነስ ቢይዘውም፥ የማይነካ ድንበር አለው። ለአብነት አቡነ ተክለሃይማኖት እግራቸው የተቆረጠው “ጦርነት ላይ በጎራዴ” መሆኑን በማስረጃ የሚያረጋግጥ መጽሃፍ ያትማል ተብሎ አይገመትም። እንደነገረኝ ከሆነ፣ “ኢትዮጵያን የሚጎዳ መጽሃፍ” አያትምም። ርግጥ ነው፥ “ኢትዮጵያን የሚጎዳ” አሳቡ አሙዋጋች ነው። “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት” ሲባል “ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፥ አማራ፣ ያማራ ባህል፥ አማርኛ፣ አረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ባንዴራ” ሆኖ ለዘመናት ኖሮአል። ኤልያስ ወገናዊ መሆኑ “የአገር ጉዳይ” ሆኖበት መሆኑን ታዝቤያለሁ። እና ታዲያ ኦሮሞ ታሪክ ጽሃፊዎች ወደ ጸሃይ አሳታሚ ብቅ ብለው አያውቁም። ባብዛኛው ገበታቸው ከRed Sea Press, ከካሳሁን ቸኮል ጋር ነው።
በቆይታዬ ከኤልያስ ጋር ምሳ በላን። አንዳንድ መጻህፍትንም በስጦታ ሰጠኝ። LMU Magazin የተባለውን የMARYMOUNT UNIVERESITY መጽሄትም ሰጠኝ። መጽሄቱ የኤልያስን አጭር ባዮግራፊ ይዞ ነበር። A LIFE IN EXILE በሚለው በዚህ ትረካ ወያኔ እንደመጣ ኤሊያስ ወደ ባሌ ተራሮች ሄዶ የትጥቅ ትግል ለመጀመር አቅዶ እንዳልተሳካለት ያወጋል። በመቀጠል ጋዜጠኛ ሆነ። ከጉዋደኞቹ ጋር “ሞገድ” የተባለች ጋዜጣ መስርቶ የወያኔን ስርአት በብእር መውጋት ቀጠለ። ባሌ ተራሮች ላይ ከመሸፈት በላይም ጋዜጠኛነቱ ወጤታማ አደረገው። እንደትረካው ኤልያስ ወደ ኤሜሪካ የሄደው ለስደት አልነበረም። አሜሪካ ሳለ የስራ ባልደረቦቹ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ምክንያት ግን ላለመመለስ ወሰነ። ቤተሰቡንም ወደ አሜሪካ ወሰደ። እና የተሳካለት አሳታሚ ሆነ።
ኤልያስ የብዙዎች ምሳሌ ነው። ጀግና ልብ ነበረው። አገሩን ይወድ ነበር። ያነበበ ሰው ነው። ለታሪክ ፋይዳ ያላቸውን ከ150 በላይ መጻህፍት አሳትሞአል። ዳሩ ግን እንዳብዛኞች እሱም ከባህር የወጣ አሳ ሆኖአል። እና ታዲያ አንዳንድ ጊዜ ትክዝ ብዬ ስለ ስደት ሳስብ አንዲት የኢሳይያስ አፈወርቂ አባባል ትዝ ትለኛለች፣ “...በአገሩ የሌለ - የትም የለም!”
1 comment:
THANK YOU !!! "THE BLACK SOIL OF ADHA"
Post a Comment