Monday, September 30, 2013

የእሬቻን በአል አከበርኩ!

 ቅዳሜ መስከረም 28, 2013 እዚህ አምስተርዳም ከተማ የእሬቻን በአል አከበርኩ። ከሶስት መቶ በላይ ሰዎች በአሉን ለማክበር መጥተው ነበር። “ያ! መሬሆ!” እያልን ወደ ውሃው ተጓዝን። ከዚያም ቢጫ አበቦች እና እርጥብ ቅጠል ውሃው ላይ አስቀመጥን። አብዛኛው የበአሉ ታዳሚ የኦሮሞን ባህላዊ ልብስ ለብሶ ነበር። ሴቶች እና ህፃናትም በብዛት ነበሩ። በአካባቢው የነበረ አንድ ሆላንዳዊ በመደነቅ አፉን ከፍቶ ትርኢቱን ይመለከት ነበር።    


የእሬቻ በአል ቅዱስ በአል እንደመሆኑ ከልጅነታችን ጀምሮ ደብረዘይት ላይ ወደ ሆራ ሃይቅ በመሄድ እናከብረው ነበር። ስለ እሬቻ በአል እውቀቱ የሌላቸው ሰዎች በሩቁ ጥንቆላ ይመስላቸዋል። ጥንቆላ ግን አይደለም።
           በኦሮሞ ህዝብ ባህል ውስጥ በርካታ ቅዱስ በአላት አሉ።
ለመጥቀስ ያህል የሚከተሉት ናቸው።
Ibsaa Oromoo ክረምት ሲወጣና ብርሃን ሲገባ የሚከበር በአል ነበር። ተለውጦ አሁን ከመስቀል በአል ጋር ተዳምሮ ይከበራል። የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ የአዲስ አመት በአል ሳይሆን አይቀርም። አከባበሩ የሚፈፀመው ደመራ በማብራት ነው።
Waree በመስቀል በአል ማግስት የሚከበር ሲሆን፣ ከብቶችን ግጠው ወደማያውቁት መስክ በመውሰድ ሳር እንዲግጡ ይደረጋል። በነጋታው ደግሞ ደመራው በተቃጠለበት ቦታ እሬቻው ይደረጋል።
Irreecha የክብር ዋጋ ነው። ለምለም ሳር ጥሩ ነገር ስለሆነ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ በምስጋና መልክ የሚቀርብ ዋጋ ማለት ነው።  በእሬቻ በአል ቡና ተፈልቶ፣ አዲስ የደረሰ የባቄላና የአተር እሸት ተቆልቶ ለቡና ቁርስ ይቀርባል። ለአዲስ ሰብል መድረስም ምስጋና ይደረጋል።
Sirna okolee dhabbannaa (የኦኮሌ ስርአት) ለመጀመሪያ ጊዜ የወለዱ ከብቶችን ለመመረቅ የሚከበር ስርአት ነው። ጊደሮች ወተታቸው ተጠራቅሞ፣ ግማሹ ተንጦ፣ ቅቤው ወጥቶ፣ ግማሹ እርጎ፣ ግማሹ አይብ ተደርጎ ቅንጬ ተሰርቶ፣ ዘመድአዝማድ ተሰብስቦ ከተመረቀ በሁዋላ ይበላል። በጥንት ዘመን ይህ ስርአት በነሃሴ ወር የሚፈፀም ነበር። ከክርስትና መምጣት በሁዋላ ግን ከመስቀል በአል ጋር ተቀላቅሎ ይከበራል።
(በቅርቡ ለንባብ በሚበቃው “የስደተኛው ማስታወሻ” በተባለው መፅሃፍ ላይ የኦሮሞን ህዝብ ነባር ባህላዊ ቅርሶች የሚነካካ በተለይም የቱለማ ገዳን በጨረፍታ የሚዳስስ አንድ ምእራፍ አካትቻለሁ። ርግጠኛ ነኝ የጫልቱ ሚደቅሳን ምእራፍ አንብባችሁ ስታበቁ መፅሃፉን አጥፋችሁ ታስቀምጡታላችሁ። ብዙ የተደበላለቀ አሳብም ወደ አእምሮአችሁ ይመጣል።)   


No comments: