Thursday, June 29, 2017

OPDO! እንደ መጥምቁ ዮሃንስ


OPDO አዴት ላይ ሲመሰረት እነ ኩማ፣ እነ ኢብራሂም መልካ፣ እነ ባጫ ደበሌ፣ ዋና አክተሮች ነበሩ። ኢብራሂም መልካ አንድ ጊዜ በሚዲያ፣ “ለኦሮሞ ህዝብ የማትሆን ኢትዮጵያ አስር ቦታ ትበጣጠስ!!” ብሎ በመናገሩ መለስ ደንግጦ አባረረው። ይህ ከሆነ 28 አመታት እንደዋዛ አልፈዋል።
ህወሃት አዴት ላይ የመሰረታት ኦህዴድ - OPDO ዛሬ በህይወት የለችም። የዛሬው OPDO በመንፈስም ሆነ በአላማ የተለየ እንደሆነ ይሰማኛል። የቀድሞውን OPDO አብርሃ ማንጁስ በቀላሉ ይነዳው ነበር። ሰለሞን ጢሞ ይቆጣው ነበር። አዲሱ ለገሰ እንደፈለገው ያንገላታው ነበር። የቀድሞዎቹ የOPDO አመራር አባላት ራሳቸውም እየተሰቃዩ ስንቱን ሲያሰቃዩ ኖረዋል። ለማይረባ ስልጣን የህዝባቸውን መከራና አበሳ አራዝመዋል። የዛሬዎቹስ? በርግጥ ካለፈው ስህተት ተምረዋል? ራሳቸውን እየሸወዱ ይሆን? ወይስ ለክብርና ለመስዋዕትነት ቆርጠው ተነስተዋል?

የምንሰማው እውነት ከሆነ የOPDO የትንሳኤ ዘመን የደረሰ ይመስላል። ህወሃትና የኦህዴድ አባላት ውስጥ ለውስጥ ትግል ላይ መሆናቸው ከተለያየ አግጣጫ ይሰማል። ፍጥጫ ላይ ናቸው። የኦህዴድ ኦሮሞዎች ነጻነትን ደህና አድርገው ቀምሰዋታል። የኦሮሞ ወጣቶች በከፈሉት መስዋእትነት የቀመሱትን ነጻነት በርካሽ ዋጋ ይወረውሩታል ተብሎ አይገመትም።
የOPDO አባላት እንደ እነ ባሮ ቱምሳ፣ እንደ አቦማ ምትኩ፣ እንደ ጃራ አባገዳ፣ እንደነ አብዱልሰመድ፣ እንደነ ማሞ መዘምር፣ እንደነ አብሼ ገርባ፣ እንደነ መገርሳ በሪ፣ እንደነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ስማቸውን የሚተክሉበት ታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመዋል። የኦሮሞ ህዝብ አብዮት እስረኛውን OPDO ፈንቅሎ የነጻነቱን መንገድ አሳይቶታል። በዚህ አብዮትም የኦህዴድ አባላት ራሳቸው ተሳታፊ ነበሩ። ዳር ቆመው ተመልካች አልነበሩም። ወያኔ ኦህዴድን እንደቀድሞው ህሊናውን አስሮ ሊነዳው መጣሩ አይቀርም። ፈታኝ ቀናት በከፍተኛ ፍጥነት በመምጣት ላይ ናቸው።
የኦሮሞ አብዮትን ተከትሎ የህወሃት አመራር “ተሳስተን ነበር” ሲል በተዘዋዋሪም ቢሆን ነግሮናል። ይህ ማለት “የታሰሩት ልክ ነበሩ” ማለት ነው። እና ታዲያ የታሰሩት ሳይፈቱ ስህተቱ እንዴት ሊታረም ይቻላል? የOPDO ቀዳሚ ጥያቄ መሆን ያለበት የታሰሩት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጉዳይ ነው። OPDO በሽርፍራፊ ጉርሻዎች ተደልሎ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ላይ ቁማር ከተጫወተ የሚከፍለው ዋጋ ውድ ይሆንበታል። ለተሰው የኦሮሞ ልጆችም ስድብ ነው።
አዲሳባ “ፊንፊኔ” እንድትባል የትግሉ ዋና ጥያቄ የሆነበት ዘመን የለም። የኦሮሞ ህዝብ የተሰዋው ፊንፊኔ ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚጠቀም ትምህርት ቤት ባለመኖሩ አይደለም። በመሰረቱ ይህም ቢሆን ሌሎች የሚሰጡት ስጦታ አይደለም። ወያኔ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰውም እጁን ተጠምዝዞና ተቀጥቅጦ እንጂ በልመና አይደለም። ዞረም ቀረ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የታሰሩት መፈታት አለባቸው። መብቱን በመጠየቁ ምክንያት የታሰረው ሰው ሳይፈታ የመብት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም።
በሚቀጥለው ዘመን ለማ መገርሳ በመላ ኦሮሚያ በኩራት ለመራመድ የዛሬው ተግባሩ ወሳኝ ይሆናል። በሄደበት ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ “ለማ! ለሜ! ለሚ! ለሜሳ!” እያለ በፍቅር ይጠራው ዘንድ ዛሬ እድል እጁ ላይ ወድቃለች። ለማ ከህወሃት ጋር ተጋፍጦ ማሸነፍ ይችል ዘንድ ግን የኦህዴድ አመራርና አባላቱ ከጎኑ ሊቆሙ ይገባል። ለማ ብቻውን ብዙ ሊገፋ አይችልም። የዙሪያው ድጋፍ ያስፈልገዋል። በዙሪያው ያሉት ደግሞ የOPDO አባላት ናቸው።
የኦሮሞ ህዝብም እንደ ህዝብ የኦህዴድን አባላት ነጥቆ ለመውሰድ በሙሉ ሃይሉ መግፋት አለበት። ህወሃት ለራሱ ሲል የዘረጋውን መዋቅር የራሱ ሊያደርገው ይችላል። ለማ መገርሳም እንደ ዮሃንስ መጥምቁ፣ “ከእኔ በሁዋላ የሚመጣውን ተመልከቱ!” እያለ በከፍተኛ ድምጽ በማወጅ መንገድ ጠራጊ ለመሆን ይበቃል።

2 comments:

Tech with Estif said...

THANK YOU !!! "THE BLACK SOIL OF ADHA"

Unknown said...

Thanks Obbo Tasfaye: I always love your critics