Wednesday, September 7, 2016

የሩንዳሳ ረጅም ታሪክ

ተወልዶ ያደገበትን ድንበር አቋርጦ በጫካማነቱ ወደሚታወቀው አካባቢ የገባው ለአደን ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል? የመጣበትን አቅጣጫ እስኪስት ድረስ ጫካው በውበቱ እየሳበ ወስዶ ወስዶ ከማህፀኑ ከተተው። እንደ ሹሩባ የተገማመደው ሰርዶ ፈረሱን ለመጋለብ ቀርቶ ለመስገር ያህል እንኳ እንቅፋት ሆነበት። ከመንደሩ ብዙ መራቁን፤ መንገድ መሳቱን እንደተገነዘበ ስጋት ቢጤ ልቡን አቋርጦ አለፈ። ፍርሃቱና ስጋቱ ግን ብዙም አልቆየ። በትር ከያዘ ካንድ ጎልማሳ ገበሬ ጋር በድንገት ተገጣጠመ። ፈረሰኛው እፎይታ ሲሰማው ገበሬው መደነቅ አደረበት።

"ጤና ይስጥልኝ ገባር!" አለ ፈረሰኛው።

ገበሬው ባርኔጣውን ብድግ አድርጎ ምላሽ ሰጠ።

ፈረሰኛውም በኩራት ተናገረ፣

"ስማኝ ገባር! ከአገሬ ለአደን ወጣሁና ጫካው ውስጥ መንገድ ሳትኩ። በል እንግዲህ ሮጥ ሮጥ እያልክ መንገዱን ምራኝ። ሁዋላ ማን መሆኔን ስታውቅ እድለኛ መሆንህን ትረዳለህ። በል ፈጠን በል!"

ገበሬው ከፊት በእግሩ፤ ፈረሰኛው ከሁዋላ በፈረስ ተከታትለው ጫካውን እያቆራረጡ ገሰገሱ። ከጮመን ወንዝ አቅጣጫ የሚነፍሰው ቀዝቃዛ ነፋስ አልፎ አልፎ ፊታቸውን እየገረፈው ብዙ እንደተጓዙ ፈረሰኛው ቅሬታውን ገለፀ፣

"ስማ ገባር! አገሬ ሳልገባ እንዳይመሽ ሰግቻለሁ። አረማመድህ አላማረኝም። ፍጥነት ጨምር።"

ገበሬው ግን ፍጥነቱን አልጨመረም። የእንግዳውን ትእዛዝ ሳይቀበል ቀረ።

"አልሰማኸኝም!? ሮጥ ሮጥ በል ብየህ ነበርኮ?"

ገበሬው ምላሽ አልሰጠም።

ጥቂት እንደተጓዙ ፈረሰኛው መልሶ ተናገረ፣

"ሰውዬው! ሳይመሽ ከመንደሬ የምደርስ ይመስልሃል?" ሲል ጠየቀ።

ገበሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ አውጥቶ ምላሽ ሰጠ፣

"አይመስለኝም። ጀምበር እየጠለቀች ነው።"

ፊትና ሁዋላ ሆነው ጉዟቸው ቀጠለ። ፈረሰኛው ስጋት አደረበት። የሚያቋርጡት ጫካ ገና አልከፈተም። ፈረሰኛው ወዴት አቅጣጫ በመጓዝ ላይ መሆናቸው አልገባውም። ሆኖም ገበሬውን ከመከተል በቀር ምርጫ አልነበረውም። የገበሬው ጥልቅ ዝምታ ግን ቀስበቀስ ይረብሸው ጀመር። በመሆኑም ያደረበትን ስጋት ለማቃለል ሲል አቀራረቡን ለማሻሻል ተገደደ፣

"ወንድሜ! ደክሞህ ሊሆን ይችላል። ልውረድልህና ፈረሱ ላይ ተቀመጥ?"

ገበሬው ባርኔጣውን በማንሳት ካመሰገነ በሁዋላ በእግሩ እንደሚሻለው ገለፀ።

እናም ጉዟቸው ቀጠለ። አእዋፍ ወደጎጇቸው ሲገቡ ታየ። የቆቅና የጉሬዛ ዜማ በርቀት ተሰማ። ለአደን የሚወጡ አነስተኛ አውሬዎች ይጠራሩ ጀመር። ከጮመን ወንዝ አቅጣጫ የሚነፍሰው ነፋስ በረታ። ጫካው ፈካ እያለ ቢሄድም ፀሃይ በመጥለቋ ምድርና ሰማይ በደንገዝጋዛማ ጥላ በስሱ ተሸፈነ። ገበሬው ባልተጨመረና ባልተቀነሰ አረማመዱ ሲጓዝ፤ የፈረሰኛው ስጋትም ከጨለማው ጋር እየበረታ ሄደ።

እንግዳው የፈረሱን ዳንጋላሳ ዳንስ ከገበሬው አረማማድ ጋር እያስተካከለ ታሪኩን ለገበሬው ነገረ፣

"የተከበሩ ወንድሜ! መቸም መተዋወቅ ደግ ነው። አባቴ የታወቁ ሰው ነበሩ። አገር ያቀኑ አርበኛ ነበሩ። የዛሬውን አያድርገውና ብዙ ገባር ነበራቸው። ስሜ ግርማቸው ይባላል።"

ገበሬው እንደገና ባርኔጣውን ብድግ አድርጎ ካከበረ በሁዋላ ስሙን ተናገረ፣

"ሩንዳሳ እባላለሁ።"

ጉዟቸው ረዝሞ፣ ጨለማው በከበደ መጠን የፈረሰኛው ትህትናም እየጨመረ ሄደ።

"መቸም በተገናኘን ጊዜ ባለማወቅ ክብርዎን በሚነካ መልኩ አንዳንድ ስድ ቃላት ከአንደበቴ አምልጠው ወጥተዋል። መቸም ይቅርታ እጠይቃለሁ።"

ገበሬው በተመሳሳይ መልኩ አሁንም ባርኔጣውን በማንሳት ትህትናውን ገለፀ። እናም ጉዟቸውን በመቀጠል ከጭቃና ከሳር ከተሰሩ ጥቂት ጎጆዎች መካከል ደረሱ።ገበሬውም እንዲህ አለ፣

"ይሄ የኔ ቤት ነው። ስለመሸ እዚህ አድረው ሲነጋ መንገድ መቀጠል ይሻልዎታል።"

የገበሬው ሚስት አጎዛ አንጥፋ እንግዳውን አስተናገደች። ከብቶቹን ወደ ግርግም እያስገቡ በመዝጋት ላይ የነበሩት የገበሬው ልጆች የእንግዳውን ፈረስ ወስደው ገብስ ሰጡት። ዶሮዎች ገና ድሮ በቆጣቸው ላይ ሰፍረዋል። የጅቦች ድምፅ በቅርብ ርቀት ተሰማ። በመጨረሻ የገበሬው ሚስት ገበታ አቀረበች። በልተውና እርጎ ጠጥተው ሲያበቁ ፈረሰኛው ከተነጠፈለት አጎዛ ላይ ጋደም ብሎ ስጋት አዘል ምስጋናውን አቀረበ፣

"ጌታዬ!" ሲል ጀመረ፣ "ጌታዬ! መቸም ውለታዎ አይረሳም። ርጋታዎ ትህትናዎ ሁሉ መቸም ቅድም የገለፅኩት ነው። እግዚሃር ያክብርልኝ።እንዳው ግን ልጠይቅዎና እዚህ ቤት በሰላም እንደማድር፤ ሌሊቱን ምንም ችግር እንደማይገጥመኝ ቃልዎን ይስጡኝ? ይማሉልኝ?"

በዚህ ንግግር ገበሬው ክፉኛ ተከፋ። ዘግየት ብሎም ምላሽ ሰጠ፣

"መጠራጠሩን ምን አመጣው? የእግዚአብሄር እንግዳ አይደሉምን?"

ከጥቂት ደቂቃዎች በሁዋላ የምድጃው እሳት ተዳፈነ። አካባቢው በከባድ ጨለማ ስር ወደቀ።የትላልቅ አውሬዎች የበረታ ድምፅ በቅርብና በሩቅ ርቀት ተሰማ። የአውሬዎቹ ድምፅ በቅርብ ርቀት ሲሰማ ገበሬውና ልጆቹ ጦርና ገጀራቸውን አፈፍ እያደረጉ ወደ ደጅ ይወጣሉ። በፋና እና በድምፅ አውሬዎችን አባረው ሲያበቁ ተመልሰው ወደ ጎጇቸው ይገባሉ። ፈረሰኛው በዚያች የገበሬ ጎጆ ጣራ ስር በሰላም ማደር ስለመቻሉ ስላልተማመነ አእምሮውን ማሳረፍ ሳይችል ብዙ ቆየ። ሊነጋጋ አካባቢ ግን ድካም ተጫጭኖት ጥቂት ሸለብ አደረገው።

ማለዳ ጀንበር ከመውጣቷ በፊት ገበሬው ፈረሰኛውን ቀሰቀሰው።

"ይበሉ ይነሱ! መንገድ ሳይነጋ ቢጀምሩት ይሻላል።"

ፈረሰኛው ደግሞ ደጋግሞ እያመሰገነ ተጣጥቦ፣ ለባብሶ፣ ቀማምሶ ፈረሱ ላይ ለመሳፈር ዝግጁ ሆነ። ገበሬውም ከልጆቹ የመጨረሻውን፣ "ቢሎ! ቢሎ!" ሲል ጠራው። ቢልሱማ ስሙ ሲጠራ ፈጥኖ በመምጣት ከአባቱ ገፅ ተከሰተ፣

"ያገራቸውን መንገድ አሳያቸው!" ሲል አዘዘ።


ቢሊሱማ እንግዳውን እየመራ ወጣ። ከጥቂት ደቂቃዎች በሁዋላም ሰማዩ መቅላት ጀመረ። ሩንዳሳም በሬዎቹን እየነዳ ወደ እርሻ ስራው አቀና። ብዙም አልቆየ። እንደ ልጃገረድ ፍልቅልቅ ብላ የምትስቅ ፀሃይ ብቅ አለች።

12 comments:

Tech with Estif said...

THANK YOU!!! "THE BLACK SOIL OF ADHA"

Anonymous said...

awesome!!

Unknown said...

Thank you Obbo Tesfaye freedom is near to the Oromo people at the grave of TPLF

Anonymous said...

Tesfaye
Des yemil treka new, gn Abyot eyefeneda ye abyot tsihufoch new kante yemitebeqew. Dem eyefesese new yalew yante tsihuf eyefesese lalew ye wegenachn dem asmelkto bihon tilq astewatsioo yadergal. Bezihu qewti seaat kewegenh gon teselfeh dimtsihin endtasema enteyqhalen.

Anonymous said...

YAGERACHEW MENGED ASAYACHEW

AS ALWAYS SIMPLE ARTICLE WITH BIG MESSAGE. I READ IT AGAIN AND AGAIN AND AGAIN........ WHAT AN ARTICLE

THANKS TESFAYE
(But waiting time is too long for us, your articles are important to us and please keep write).

Yonathan A

Unknown said...

Galatoomi Gadaa keenya

Nebro said...

Teret teret ,yelam beret... people expect more of intelectual writings, not "yemerkana" story, grow up Tesfaye !

Anonymous said...

Me too
I read read and read again and understand the message.
Tesfu

Anonymous said...

ያገራቸውን መንገድ አሳያቸው!"

We start to show weyane the way to Dedebit from Oromia and our Amhara brothers follow us to show WE Y A NE the way to Inderta ana aba guna from Gonder.

Belayneh

Anonymous said...

If Tesfaye is not an intellectual writer why you come to this blog? You come here to read intellectual writing Period.

Don't say teret teret

Anonymous said...


"ሩንዳሳ እባላለሁ።

"ይሄ የኔ ቤት ነው ጮመን ወንዝ አገሬ ነው። 


Amansiis said...

በአሥር ትላልቅ መፅሀፍት ማለቅ የማይችል ታሪክ እንዲህ አሣጥረህ ለሚገባው በሚገባው መልኩ ሥላካፈልከን ምሥጋናዬ እንደተለመደው ትልቅ ነው።