Thursday, March 17, 2016

“ይቅርታ” ወይም “ሰላም”



ሃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ያደረጉት ቃለመጠይቅ አነጋጋሪ ነበር። ከኦሮሞ ህዝብ አመፅ ጋር በተያያዘ የሰነበተውን ችግር ሌላ አካል ላይ ማላከክ እንደማይገባ መናገራቸው ከኢህአዴግ ጠባይ አንፃር ያልተለመደ ነበር። በውስጥ ባለ ችግር ምክንያት የህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ህዝብና መንግስት ተቃቅረው ጉዳዩ ወደ ግጭት ደረጃ መድረሱን ማመናቸው አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። ችግሩ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን መግለፅ መቻላቸው ይደነቃል። ሃይለማርያም በዚህ ደረጃ ችግሩን አምነውና ተቀብለው ሲያበቁ፤ በመጨረሻ ለተፈጠረው ችግር በጥቅሉ ህዝብን ይቅርታ ጠይቀዋል። ይቅርታ ጥየቃው ካንገት በላይ ነው ወይስ ካንገት በታች ለጊዜው ባናውቅም፤ ይቅርታ መጠየቅ በራሱ ስልጣኔ ነው።

እንግዲህ በመቀጠል ወደ ዝርዝር ጉዳይ እንግባ። 

ሃይለማርያምይቅርታ ሲጠይቁ በመሰረቱ ምን ማለታቸው ነው? ከዚህ በሁዋላ ኢትዮጵያ ላይ በህጉ መሰረት ሰላማዊ ተቃውሞ ማካሄድ ተፈቅዶአል ማለት ነው? ከዚህ በሁዋላ የፌደራል ፖሊስ ሰላማዊ ሰዎችን በየጎዳናው አይገድልም? ባለፉት አራት ወራት እና ከዚያም በፊት በየጎዳናው ለተገደሉት ንፁሃን ዜጎች ወላጆችና ቤተሰብ ካሳ ይሰጣል? ንፁሃን ዜጎችን የገደሉና ያስገደሉ ለፍርድ ይቀርባሉ? የታሰሩት በአስር ሺዎች የሚገመቱ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ? መሬታቸው ተነጥቆ ለተፈናቀሉ ገበሬዎች ተገቢው ካሳ ተከፍሎ እንዲቋቋሙ ይደረጋል?ይቅርታውን ተከትሎ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ አንዳችም ያሉት ነገር የለም። በደፈናው ሸውዶ ለማለፍ የተደረገ የለበጣ ይቅርታከሆነ ቅዳሴና ዳንኪራንእንደመደባለቅ ይቆጠራል

ከአንድ ሰው ጋር ስለዚሁ ጉዳይ ስንወያይ፣ “ሃይለማርያም ይቅርታ ጠየ ለማለት አይቻልም።ይቅርታውን መልአፍርሶታል።” አለኝ። ሌላው ደግሞ፣ “ሃይለማርያም ከዚህ ቀደም አስመራ ሄጄ ከኢሳይያስ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ’ ሲሉ እንደተናገረው አሁንም የግሉን ይቅርታ ደባልይሆናል።” አለ። ከዚህ በተጨማሪ “የይቅርታው ቃል በአሜሪካኖች አስገዳጅነት በህወሃት እውቅና የመጣ ነው።” የሚል የውስጥ አዋቂ መረጃም ሰምቻለሁ። ከአስተያየቶች ሁሉ “ይቅርታ” የምትለው ቃል በአሜሪካኖች ተፅእኖ የተነገረች ልትሆን መቻሏ ወደ እውነት የሚጠጋ ይመስለኛል። ሲፃፍ እንደሰነበተው ወያኔ ችግር ውስጥ መገኘቱ አከራካሪ አይደለም። አስረጅ ሊሆን ከሚችለው መካከል፣ “ከኦሮሞ ህዝብ አመፅ ጀርባ የኤርትራ እና የግብፅ ተላላኪዎች አሉ” የሚለውን ክስ ለመተው መገደዳቸው አንዱ ነው። የኦሮሞ ህዝብ አመፅ መነሻ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ማመን እስከዛሬ ጌታቸው ረዳ ሲነግረን የነበረውን ይቃረናል። 

ርግጥ ነው፤ ሃይለማርያም ይቅርታ መጠየቅ ጋር በተያያዘ ከሚሰሙጭምጭምታዎች ዋናው የአሜሪካኖች ተፅእኖ ሚዛን የሚደፋ መስሎ መታየቱ ነው። የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ“ሰላም” የተባለው የማሸማገል ሂደትም የቀጠለ በመሆኑ ምን መልክ ይዞ ይፋ እንደሚሆን በቀጣዩ ጊዜያት የምንሰማው ይሆናል። በአንድ ወቅት CUD የተባለውን ቅንጅት ይመሩ የነበሩ ሰዎች በፕሮፌሰር ኤፍሬም አሸማጋይነት ከእስርቤት ከወጡ በሁዋላ የወያኔ ፍላጎት እንደምንም ተያይዘው ከአገር እንዲወጡለት መንገድ መክፈት ነበር። በርግጥም አብዛኞቹ ባገኙት እድል ሁሉ ተጠቅመው የታገሉላትን አገር ትተው እንደማይመለሱ ሆነው ርቀው ሄደዋል። ይህ ለህወሃት አገዛዝጥሩ እድል ነበር። አብዛኞቹየCUD ሰዎች ከኮበለሉ በሁዋላ ወያኔ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉትን ነጥሎ መምታት አልተቸገረም። 

ህወሃት ቅንጅትን አዳክሞ ባጠፋው መንገድ የኦሮሞ አማፅያንን በዚያው ዘዴ ለማኮላሸት ማሰቡ ገና ያልተፈፀመ በሂደት ላይ ያለ ተግባር ነው። እንደሚሰማው የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ እስረኞችን ለመፍታት ለአሜሪካኖቹ ቃል ገብቶ ከሰነበተ እንግዲህ ይቅርታዋ እንደምንምተነግራለች።  እስረኞችን መፍታግን ገና አልተፈፀመም። እንደ ውስጥ አዋቂዎች ጥቆማ ከሆነ በእስርቤት ካጎሯቸው በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ኦሮሞ እስረኞች መካከል የአመፁ አስተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የገመቷቸውን በመለየት ስራ ተጠምደዋል። አመፁን ያስተባብራሉ ብለው የሚገምቷቸውን ለይተው ካበቁ በሁዋላ ወደ ስደት የሚሄዱበትን መንገድ ያመቻቻሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህን ማድረግ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ያዳክማል፤ ስርአቱ ትንፋሽ እንዲያገኝም ፋታ ይሰጠዋል ብለው ቢያስቡ ከልምዳቸው አንፃር ስህተት አይሆንም። የነቃው እና የተደራጀው ግለሰብ ከሜዳው ገለል ካለ አመፁ ጠቅልሎ ባይቆም እንኳ ፋታ ሊገኝ ይችላል።በርግጥ እንደ እስክንድር ነጋ፤ እንደ በቀለ ገርባ ለመኮብለል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሲገጥሙ ቀመሩ ተገላቢጦሽ ይሆናል። 

የኦሮሚያ ወጣቶች ሴራውን ባለመረዳት ለአዲስ ዙር ስደት ከተነሱ ‘በአገሩ የሌለ - የትም የለም።’ እንደሚባለው ለህወሃት ድል ይሆናል።ኮብላዮች ድጋፍ ሰጪ ከመሆን ያለፈ አቅም አይኖራቸውም።የኦሮሞ ህዝብ አሁን ከደረሰበት የተሰሚነት አቅም ላይ እንዲደርስ ያደረጉት በግንባር ቀደምትነት ተጋፍጠው መስዋእትነት የከፈሉት ጥቂት ወጣቶች ናቸው። ድጋፍ ሰጪ ስደተኛ የማድረግ ችሎታው በጣም ውሱን ነው። ሃርቫርድ ከሚገኝ አንድ ተራ ፕሮፌሰር፤ ሃሮማያ የሚገኝ አንድ ተራ የገበሬ ልጅ የተሻለ የማድረግ ችሎታ አለው።ህወሃት ከዳያስፖራ ይልቅ አጠገቡ ያሉትን ተራ ዜጎች ይሰጋል። ስለዚህ የማስቸገር ብቃት ያላቸው ይኮበልሉ ዘንድ ተግቶ ይሰራል። ማሰርና መግደል የህወሃት የመጀመሪያ ምርጫ ሆነው አያውቁም። የኮበለለ ሁሉ የወያኔን የመጀመሪያ ምርጫ እንደተቀበለና እንደተሸወደ ማወቅ አለበት።

ባለፈው ሳምንት “የቅዳሜ ማስታወሻ” ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅን በጨረፍታም ቢሆን ነካ አድርጌያቸው ነበር።በላኩልኝ ኢሜይል ስለርሳቸው ያለኝ ግንዛቤ ስህተት መሆኑን ጠቁመውኛል። እርሳቸው እንደገመቱት ሳይሆን ስለ ፕሮፌሰሩ ብዙም ባይሆን ጥቂት አውቃለሁ። የት ከማን እንደተወለዱ የት ምን እንደተማሩየት ምን እንደሚያስተምሩ አውቃለሁ። ደረጀ ደሬሳ በአጤ ሃይለስላሴ ዘመን በወቅቱ የ31 አመት ጎረምሳ ለነበሩትለአቶ ኤፍሬም ይስሃቅ የፃፈውን መወድስም ኢትዮጵያ ሳለሁአንብቤያለሁ። በተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘመን ለአገራቸው ብዙ ቁምነገር የሰሩ ሰው መሆናቸውን ቀደም ብዬም አውቅ ነበር። ሽማግሌው ፕሮፌሰር በጎልማሳነታቸው ዘመን ለደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች መብት መከበር መታገላቸውን በርግጥ አላውቅ ነበር።ዞረም ቀረ የተሰራው መልካም ነገር ሁሉ በቦታው አለ። ታሪክ አይረሳውም፤ ታሪክ ያመሰግናቸዋል።ፕሮፌሰሩ የአባት አገራቸው ታማኝ ልጅ ቢሆኑም፤ መወለድ ቋንቋ ነውና ልክ እንደኔው እሳቸውም የትውልድ አገራቸውን እንደሚወዱ እረዳለሁ። 

ፕሮፌሰር ኤፍሬም በደርግ ውድቀት ማግስት የመሸጋገሪያው መንግስት ምስረታ ላይ፣ ታምራት ላይኔን ለማሞገስ፣ “ተአምራት ለአይኔ፣ ተአምር በአይኔ አየሁ” ብለው ቅኔ ሲቀኙ ደማካጨበጨቡላቸው አንዱ እንደነበርኩ አልክድም። በወቅቱ ሁላችንም ተአምራት በአይናችን ያየን መስሎን ነበር። ታምራትና መለስ የተሸፈነ ጠባያቸው ሳይገለጥ ጥቂት አመታት እንኳ መጓዝ እንደማይችሉ አልገመትንም ነበር። ጃኬትና መኪና ወደ ማማረጥ ይገባሉ ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። የሆነው ሆኖ የስካሩ አቧራ ገለል ሲል ፕሮፌሰር ኤፍሬም በአይናቸው ተአምራት ሳይሆን መቅሰፍት ነበር ያዩት። ያም ሆኖ ወዳጅነታቸውን ከወያኔ ጋር ቀጥለዋል።እዚህ ላይ እንግዲህ መነፅራችንን ዝቅ አድርገን፣ “ጤናይስጥልኝ ፕሮፌሰር!” ለማለት እንገደዳለን።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ የኦሮሞን ህዝብ ከገዢው ግንባር ጋር ለማስታረቅ በሚያደርጉት ሙከራ፣ “ሰላም” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ “የማን ሰላም?” የሚለውንም ጥያቄ ይመልሱት ዘንድ ይጠበቃል።ሰላምን ለማስገኘት ሽምግልና ከመጀመራቸው በፊት “ፀረ ሰላም ማነው? ለሰላም ጠንቅ የሆነው ማነው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽማግኘት ይገባል። የቀድሞ በጎ ስራ ለዛሬው ስህተት ላጲስ ሆኖ አያገለግልም። “ሰላም ወዳድ” የሚለው ማእረግ “አሻጥረኛ”  ወደሚል ከተለወጠ ለመመለስ ያስቸግራል። የኦሮሞ ህዝብ በአገሩ ላይ የተረጋገጠ ሰላም ለማግኘት መስዋእትነት መክፈል እንዳለበት የተረዳበት ጊዜ ላይ ነው። በርግጥም የአዲሱ ትውልድ መሪ መፈክር አንድ ብቻ ሆኖአል። ይህም፣ “ዛሬ አንድ ነገር ማድረግ አለብን። ወይም ደግሞ መሞት አለብን!” የሚል ነው። እና ማገዙ ካልተቻለ ቢያንስ “እንኳን ለዚህ አበቃችሁ!” ማለት ይገባል።

ርግጥ ነው፤ “የሰላም መጥፎ፣  የጦርነት ጥሩ የለውም” የሚለው ነባር አባባል በጥቅሉ ተቀባይነት አለው። ልጇ የሞተባት እናት፤ አባቱ የሞተበት ልጅ ሃዘን ላይ ናቸው። ሃዘናቸውን ለመረዳት እግራችንን እነርሱ ጫማ ውስጥ መጨመር ይገባል። ቢሆንም ግን ለሰላም ሲባል ሰላምን ለማደፍረስ፤ ጦርነትን ለማስወገድ ጦርነት መለኮስ ግዴታ ሆኖ ሊመጣ ይችላል። ሲደፈርስ በርግጥ ብዙ ህይወት ይቀጠፋል። ባይሆን ጥሩ ነበር። ህይወት ሳይከፈል የብዙሃን ሰላም የማይገኝ ከሆነ ግን መደፍረሱ ግድ ይሆናል። ህይወት በሚቀጠፍበት መንገድ ብቻ ማለፍ ግድ መሆኑ ያሳዝናል። በጦርነት ድል ቢገኝም እንኳ ከድሉ ባሻገር አሸናፊውም ልክ እንደ ተሸናፊው እኩል ኪሳራ ይቀበላል። ሰላም አንፃራዊ ነው። በሚዛናዊ መነፅር ስንመለከተው ዚምቧቡዌ ከቀድሞ ሰላሟ ይልቅ የአሁኑ መተራመሷ ይሻላት ይሆናል። በዚህ የዚምቧቤ መተራመስ ውስጥ 300 ሺህ የአገሬው ሰዎች ከዘበኛነትና ከግርድና ስራ ተላቀው ባለመሬት መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም። የኦሮሞ ወጣቶች በዚህ ዘመን የተተወላቸው ስራ በተነጠቀ መሬታቸው ላይ ዘበኝነት መቀጠር ሆኖአል። ከመሬታቸው የተፈናቀሉ የገበሬ ልጆች በዘበኛነት የስራ ዘርፍ አዲሳባን እንደወረሩ፣ በበረንዳ አዳሪነት ከተማዋን እንዳጥለቀለቁ  በቂ መረጃ አለ። እነዚህ ወጣቶች ከጥቂት አመታት በፊት ባለመሬት ነበሩ። ሃብታም መሬት ያርሱ ነበር። ሳሞራ ማሼል ስልጣኑን በያዘባት ሌሊት ያንን ዝነኛ አዋጅ ያወጀው የነፃነትን የተሟላ ትርጉም ለወገኖቹ ለማቅመስ ነበር። ነፃነት ሲባል የከበርቴ ሰዎች ዘበኛ ሆነህ መለፍለፍ መቻል ማለት አይደለም። ነፃነት ከመሬት ባለቤትነት ይጀምራል። እና ሞዛምቢካውያን ከነሙሉ ችግራቸው ዛሬም ቢሆን ሳሞራን በበጎ ያስታውሱታል።  

የኦሮሞ ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስርአቱ የጫነበትን የሰቆቃ ህይወት እየተቃወመ ረጅም ተጉዟል። ሸክሙ ሲበዛበት ግን ቀንበሩን ወረወረና አታላዩን ሰላምና ፀጥታ ክፉኛ አደፈረሰው። የህልውና ጉዳይ ሆነበት። አይኑ እያየ የማያውቃቸው ሰዎች መጥተው የአያቱን መሬት ሲሸጡ ሲመለከት የሰላም ትርጉሙ ጠፋበት። መሞትን መረጠ። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን ሰው “ለሰላም ሲባል”፤ “ለአንድነት ሲባል” ብለህ ልታግባባው አትችልም። አይሰማህም። በአንድ ወቅት የOPDO ምክትል ሊቀመንበር እንደነበረው እንደ ኢብራሂም መልካ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ለኦሮሞ ያልሆነች ኢትዮጵያ አስር ቦታ ትበጣጠስ!!” ሊልህ ይችላል። በመሆኑም ፕሮፌሰር ኤፍሬም ለማን ጥቅም እየሰሩ እንዳሉ ማወቅ አለባቸው። ለኢትዮጵያ አንድነት? ለተጨቆኑ ህዝቦች ሰላም? ወይስ ለአንድ ቡድን ስልጣን? ምላሹ ለህሊናቸው ይሁን።
የጃዋር መሃመድን መረጃ ከያዝን ሌላው ይቆይልንና ባለፉት አራት ወራት በኦሮሚያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 500 አሻቅቦአል። ይህ ብቻውን እንኳ ለወያኔ ትልቅ እዳ ነው። ክፍያው ሊቸግር ይችላል። የህይወት እዳ ወለዱ ውድ ነው። ሃይለማርያም በቅርቡ ሴት ልጃቸውን በሞቀ ሰርግ ድረዋል። ሟቾቹ ወጣቶች በተመሳሳይ ለወግ ለማእረግ እንዲበቁ ወላጆቻቸው ይመኙ ነበር። ልጆቻቸውን ያጡ፣ አባታቸውን የተነጠቁ ወገኖች ሃዘኑን አይችሉትም። ሃይለማርያም ይቅርታ የጠየቁት በራሳቸው ተነሳሽነት ከሆነ ከዚያም በላይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ርግጥ ነው፤ “የኦሮሚያ አመፅ” የሚለው የጨዋታ ካርድ ላለፉት አራት ወራት ከፖለቲካ ሜዳው ላይ ሊወርድ አልቻለም። ከቀዳሚ ዜናነቱ ሊገፈተር አልቻለም።ሰበር ዜና ከመሆን ሊታቀብ አልቻለም።ሃይለማርያም የበታች አለቆቻቸውን ስነልቦና መረዳት ይጠበቅባቸዋል። አባይ ፀሃዬ እና ስብሃት ነጋ “ጥቂት ታገስ! ከዚያም ጊዜ ጠብቀህ የጨዋታውን ካርድ ቀይረው” የሚለውን የሰርቫንቴስ አባባል ደጋግመውም ይጠቀሙበታል። የ“ይቅርታ” እና የ“ሰላም” ወጎች ትእግስት ምእራፍ ሲሆኑ፤ ከረምረም ብለው የጨዋታውን ካርድ ለመቀየር መሸጋገሪያ ይሆናሉ። ያንጊዜ ጊሎቲን አንገት ቆረጣውን እንዳዲስ ይጀምራል። 

በመጨረሻ አንድ ነጥብ ላይ ላስምር። የኦሮሞ ህዝብ እየከፈለ ያለው የህይወት መስዋእትነት ኪሳራ አይደለም። ግብና አላማ አለው። ለመጪው ትውልድ እየተከፈለ ያለ የክብር ዋጋ ነው። እና የኦሮሞ ህዝብ ጨክኖ እንደጀመረ ከመግፋት በቀር አማራጭ የለውም። ወደሁዋላ ማየት እንደገና መቶ አመታት ሊያስተኛ ይችላል። መስዋእትነቱን አያስቀረውም። ከመሬት መፈናቀሉን፣ ስደቱን አያስቀረውም። የኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ህዝብ እንደመሆኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን አስተባብሮ፣ አቅፎ ወደ ተሻለው ዘመን የመጓዝ ብቃቱና ችሎታው አለው። ያለ ኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያ ምትባል አገር የለችም። እና የኦሮሞ ህዝብ ራሱን ነፃ ከማውጣት ባሻገር ከባድ ሃላፊነት አለበት። የተረጋገጠውን ሰላም ለማግኘትና በረጅሙ ለማረፍ ጨለማማውን ጫካ በድፍረት ማለፍ ይገባዋል። ይቻለዋልም። አሳምሮ ይቻለዋል። ታግለው ነፃ የወጡ የአለም ህዝቦች ታሪክ የሚነግረን ይህንኑ ነው።

የቅዳሜማስታወሻ   Gadaa Ghebreab  ttgebreab@gmail.com  www.tgindex.blogspot.com   March 17  2016

6 comments:

Tech with Estif said...

Thank You....."THE BLACK SOIL OF ADHA"!

asba said...

Galatoomi Gadaa- Miif jiraadhu. Yoo rabbi jedhe Bishooftuutti si argina.

Anonymous said...

Most Oromos don't have any peace with any one and the current upraising might have been Pulled/pushed by some of OPDOs. Oromos mostly talk about that they are majority and they have vast land although we know how they acquired the land , over 50% of the the current population is also due to Gudifacha, Naturalization and other reasons. So over 50% are floating on the air with identity crises and simply they go with the wind direction. They don't have commitment to do achieve some goal. So please if you disturb yourself with the Oromo issue you get gastric alcer or brain cancer. Go back and read history of Oromos struggle nothing since Tadese Biru. Yo are excellent writer (Tesfaye) but it is miserable that you are wresting your time for the sake of Oromos let the Oromos do their Home work and you do your own bussness such as writing on past history, there are many an taped history of Ethiopia please dig this. My advise also also please do not side the Eritrean Government.They have taken their land and still their mind is at Addis Ababa why they also think that the other Ethiopian people are foolish and they are using Oromos as their future pupet government. That sounds good to you? It is disgusting that after fighting all that 32 years and again nothing has changed in their country still they are in war with us why?

Regards
Teyib

doni said...

ኢትዮ..…አማራ

ሰንደቃላማችን ከፍ ሲል ለዓለም
ሰማሁሽ ስትይ ኢትዮጲያዊ ቀለም
በራስሽ ፈጠራ ቀለሙን ቀማሚ
መሰረቱን ንደሽ ጣሪያዉን ልታቆሚ
………………እዉነትን ስታሚ
………………..ቅጥፈትን ስትሰሚ
ደምቆ እንዳይታይ ኢትዮጲያዊ ቀለም
ጦሰኛዋ አንቺ ነሽ ሌላ ምክኒያት የለም
ትግሬ ነዉ ኦሮሞ?
ወላይታ ሲዳሞ?
አፋር ነዉ አደሬ?
በትምከት ፉካሬ
ማነዉ ያመሰዉ አገሬን?
እንዳንቺ አስተምህሮት
አንቺና ኢትዮጲያ ብቸኛ ወዳጂ
ሌላዉ ታዛቢ ነዉ ሊያዉም በግዳጅ
ዜግነት ለማግኘት ያንቺ መመዘኛ
ከቤሔር አማራ ከቋንቋ አማረኛ
ተፈጥሮ ብትከዳሽ ሆነሽ ነጭ ደሃ
ከእንስራሽ ብታጪ የምትጠጭዉ ዉሃ
የታሪክ አሻራ ድንጋዩን ክበሺ
ማንም ሳይደርስብሽ የምትናከሺ
በቅጥፈት ብዕርሽ ከትበሽ ከብራና
የእዉነት ጀንበር ወጥታ ሲገለጥ ገመና
ቀለሙም ተነነ…..……….ታሪኩም ተናደ
……………………………….ሳይቀር ለናሙና
የተካበ ድንጋይ ሲተረክ ለዓለም
ተንዶ አገኘሁት ኢትዮጵያዊ ቀለም
እንደሕዝባችን ፍቅር ጎልቶ እንዳልደመቀ
የትምክህት ምሶሶ በጉራ ወደቀ
አንድነት አይመጣም በከንቱ ፉከራ
ጥላቢስ እያለ ኢትዮ……..…… ተራራ
…………………….ኢትዮ…………... አማራ
By Doni Dan

Anonymous said...

Teyib, you seem to be in identity crisis yourself. It is not time to hear from you such a lame idea and even you don't deserve to comment about the Oromos. They are big nations with big vision. Why you and the person like remain busy hating the Oromos while they are feeding you with comfort. Go to Oromos rural, you can find any ethnic group living comfortably there. But go to the Amaras' or Tigres' or Somales'rural, can you find any Oromo farmer? They automatically kick him out or even kill mercilessly. Doing all these for them, they name them 'tebaboch' 'zeregnoch'...etc. Nothing to expect the blind, anyway!

Unknown said...

መች ይሆን ዘር ቀለም ምንትስ ቅብርጥሱን ትተን ሰው የደረሰበት ለመድረስ የምንቀናው ? ምናለ አሁን ተኝቼ ከሺህ ዓመት በኅላ በነቃሁ !!! ያኔ መቼስ ሰው በሰውነቱ ብቻ እንጅ በትርፋትርፉ የማይለካበት ዘመን እንደሚሆን አልጠራጠርም።