Wednesday, March 9, 2016

ፍርሃትም ይሸነፋል

       ዝነኛው አሸማጋይ ፕሮፌሰር ይስሃቅ ኤፍሬም መሰንበቻውን ስራ እንደበዛባቸው ተሰምቷል። የኦሮሞን ህዝብ አመፅና ጥያቄ በሰላም ለመጨረስ እዚህም እዚያም እየደዋወሉ ልብ የሚነኩ እግዚአብሄራዊ ቃላት ተናግረዋል። የፕሮፌሰሩ ጥረት በደፈናው የሚነቀፍ ባይሆንም አይሳካላቸውም። የሽማግሌው የእርቅ መንገድ ጥሎ ማለፍ ይዘት እንዳለው ካለፈ ድርጊታቸው ትምህርት ተገኝቷል። በተጨማሪ ድርድር ወይም እርቅ ሲታሰብ መላ የኢትዮጵያን ህዝብ የመብት ጥያቄዎች ታሳቢ በማድረግ እንጂ፤ ጉልበት ካገኘው  ሃይል ጋር ብቻ የመደራደር ዝንባሌ ያለፈውን ስህተት መድገም ይሆናል። በመሰረቱ ወያኔ በስውር ሽማግሌ መላክ መጀመሩ ጊዜ ለመግዛት ካልሆነ ከልብ እርቅና መደራደር ፈልጎ እንደማይሆን ይገመታል። ከፋፍሎ የማዳከም የህወሃት አካሄድ ገና ድሮ ተባኖበታል።
          ህወሃት ምንም እንኳ ላይ ላዩን የተረጋጋ ለመምሰል ቢሞክርም ውስጡ መበጥበጡ ይሰማል። አለመግባባት ባንዣበባቸው ስብሰባዎች እየታመሰ ከርሞአል። ይህን ስፅፍ ስብሰባዎቹ ገና አልተቋጩም። ቀደም ሲል በኢህአዴግ ስብሰባዎች ላይ የOLFን ወይም የግንቦት7ን ስም በበጎ ማንሳት የማይታሰብ ነበር። አሁን ተለምዶአል። የህወሃት ሰዎች አጋር እና አባል ድርጅቶችን ወደ ማባበል ደረጃ ዝቅ ብለዋል። ይህን እውነት የገመገሙ የወያኔ ወዳጆች ህወሓት ከገጠመው ቀውስ እንዲያገግም ተግተው እየሰሩ ነው። የህወሃትን ውስጣዊ ቀውስ የሚጠቁሙ መረጃዎች ከጥቂት በላይ ናቸው። ለአብነት የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ኮምፕዩተሮች የመዘረፍ ምክንያት ተራ ጉዳይ አይደለም። በሳሞራ የኑስ የሚመራው የመከላከያ ካውንስል ኦሮሚያን ማስተዳደር መጀመሩ ትልቅ ርእሰ ጉዳይ ነው። የተከሰተውን የረሃብ ችግር ለመፍታት በሚል ስም አሜሪካኖች በገፍ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ሾላ በድፍን ነው። “የኦሮሚያ አመፅ” የሚለው አባባል “የኢትዮጵያ አመፅ” ወደሚል ማደጉ የመሳሰሉት ርእሰ ጉዳዮች ህወሃት የመኖር ግዳጁን እንደፈፀመ፤ ነዳጁን እንደጨረሰ የሚጠቁሙ ሆነዋል።

በርግጥ ወያኔ ለመውደቅ አንድ ሃሙስ ብቻ እንደቀረው ከብዙ አመታት በፊት ጀምሮ ሲፃፍ ነበር። ዛሬም እየፃፍን ነው። ወያኔ ግን ሳይወድቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሃሙሶች እንደዋዛ አልፈዋል። ትንበያዎቹ የተሳሳቱ ነበሩ ወይስ ሌላ ምክንያት አለ? ሳስበው ጉዳዩ የትንበያዎች ስህተት አይመስለኝም። የወያኔ ስርአት አፈናውን እንዲያቆም ማስገደድ የሚቻልባቸው ጥቂት እድሎች በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች አምልጠዋል። ወያኔም፣ “በስብሰናል! ከሞት አፋፍ ላይ ቆመናል!” ብሎ ራሱን የገመገመባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ካልተገፋ ግን የበሰበሰ ግድግዳ እንደቆመ ይቆያል። አሁን እነሆ ጊዜው ደረሰ። “ቻዎ TPLF” የሚሉ ስንብቶች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው። ሃሰን ሁሴን ከሚኒሶታ ህወሃትን የተሰናበተው በምርጥ የአማርኛ ግጥም ነበር። የቀዌሳ የልጅ ልጅ ሎሬት ፀጋዬ ትዝ እስኪለኝ ሃሰን ሁሴን በአማርኛ ቋንቋ ተቀኘ። በረጅም ግጥሙ ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኞች ነበሩበት
ገናናነቱ መስሎት የዘላለም - የዘወትር
ኮትኮቶ ያፈራው ፍራቻ
አቻውን የማያገኝ መስሎት - በሞት
ሞትም ተበራክቶ - መካን ሞትም ሳያመክን
ሃያል ቁጣን ወለደና - ጊዜ አይቀር የለና
ሳይታሰብ እንደ ደራሽ - የበጋ ጎርፍ - ከተፍ ብሎ ደረሰና
ክምሩም ካናት ቁልቁል መናድ ጀመረና...
 
 የኦሮሚያ አመፅ ቀጥሎአል። ተዳፍኖ ሊቆም እንደሚችል ይገመት የነበረበት ጊዜ አልፎአል። ‘አመፁ ይቆማል’ ብሎ ከመጠርጠር ይልቅ፤ አመፁ ወደ ሌሎች ክልሎች ሊስፋፋ እንደሚችል መናገሩ ወደ እውነት የቀረበ ሆኖአል። በርግጥ የወያኔ አመራር ይህን እውነት በአደባባይ ባያምንም ኦሮሚያ በመከላከያ ካውንስል እንድትመራ ለጄኔራል ሳሞራ ትእዛዝ መስጠቱ ጉዳዩ ከቁጥጥራቸው ውጭ እንደሄደባቸው የሚጠቁም ነው።
 ኦሮሚያን አገላብጦ እንዲጠብስ ሃላፊነት ከተሰጠው የመከላከያ ካውንስል መካከል አንድ ኦሮሞ እንኳ አልተጨመረም። በንጉሱም ሆነ በደርግ ዘመናት ኦሮሞ በጦር አዛዥነት ችሎታው አይታማም ነበር። ‘ተሰጥኦቸው ነው’ እስኪባል ድረስ ጄኔራልነት የኦሮሞዎች ነበር። ከታደሰ ብሩ አንስቶ እስከ ረጋሳ ጅማ፤ ከቁሲ ዲነግዴ እስከ መርእድ ንጉሴ፤ ከገበየሁ ጉርሙ እስከ ደምሴ ቡልቶ፣ ከጃጋማ ኬሎ እስከ አበራ አበበ ከሁለት ደርዘን በላይ ሙያውን የሚያውቁ ኦሮሞ ጄኔራል መኮንኖችን መጥራት ይቻላል። ዛሬ ተገላቢጦሽ ሆኗል። ሌሎች ከኮሎኔልነት በላይ ከፍ ማለት አቀበት ሆኖባቸዋል። በወያኔ መከላከያ ውስጥ የሚገኙ አማራና ኦሮሞ ከፍተኛ መኮንኖች አጫዋችና በሶ በጥባጭ ሆነው ቀርተዋል። የመከላከያ ካውንስሉን ከሚመሩት አስራ አንድ ጄኔራሎች ዘጠኙ የህወሃት አባላት ሲሆኑ፤ እነርሱም ሳሞራ የኑስ፣ ዮሃንስ ገ/መስቀል፣ ሰአረ መኮንን፣ ገብረ አድሃኖም፣ ኢብራሂም አብዱል ጀሊል፣ መሃሪ ዘውዴ፣ አብርሃ ወ/ማርያም፣ ፍስሃ ኪዳኑ እና ዮሃንስ ገ/ሚካኤል ናቸው። ቀሪዎች ሁለቱ አማራና አገው ናቸው። እነሱም አደም መሃመድና ገብራት አየለ ናቸው። ሳሞራ ባለፈው ሳምንት ከተጠቀሱት ጄኔራል መኮንኖች መካከል የህወሃት አባል የሆኑ ስድስቱን (ስታፍ ጄኔራል መኮንኖች) ሰብስቦ በኦሮሚያ ጉዳይ ላይ አነጋግሯቸዋል። ሳሞራ በስብሰባው ላይ፣
“እያንዳንዳችሁ የምታደርጉት ውጊያ ለራሳችሁ ለህልውናችሁ መሆኑን ተረዱ። አመፁን ማክሸፍ ካልቻልን የመጀመሪያው የጥቃት ኢላማ እኛ ነን። አደጋ ላይ ነን!” ሲል በግልፅ እንደነገራቸው ተሰምቷል።
እነዚህ ጄኔራል መኮንኖችም በመቀጠል የሳሞራን ቃል እየጠቀሱ ማስጠንቀቂያውን በጠባብ ክልል ወደታች አውርደውታል። ሳሞራ አልተሳሳተም። እውነት ብሏል። የትግራይ ህዝብ ሳይሆን፤ የህወሃት መሪዎች አደጋ ላይ ናቸው። ካልታጠቀ ህዝብ ጋር ከመዋጋት፤ ከለየለት ታንከኛና መድፈኛ ሰራዊት ጋር መዋጋት በእጅጉ የቀለለ ነው። ወያኔ በለመደው የውጊያ ስልት እየተዋጋ አይደለም። በወታደራዊ አነጋገር ልጠቀምና የኦሮሞ ህዝብ ራሱ በመረጠው ስልት፣ ራሱ በመረጠው ጊዜ እና ራሱ በመረጠው ሜዳ ላይ ከወያኔ ሰራዊት ጋር እየተፋለመ ነው። ይህ ለኦሮሞ ህዝብ ድል ነው። OPDO ፈርሶ በምትኩ ኦሮሚያን በህወሃት ጄኔራሎች እዝ ስር እንዲያስገቡ ማስገደዳቸው በእውነቱ ትልቅ ድል ነው። ለወያኔ በአንፃሩ የፍፃሜው መጀመሪያ ነው።  
ህወሃት ከምስረታው ጀምሮ በታሪክ ጎዳና ላይ እየሮጠ ነው። እየወደቀ እየተነሳ ሲሮጥ 42 አመታት ሞልቶታል። መቸም አንበሳና ሚዳቋም በማለዳ ተነስተው ሁለቱም ይሮጣሉ። ምክንያቱም ህይወት ከመሮጥ እና ራስን ከመተካት ያለፈ ሌላ ልዩ ተልእኮ የላትም። ወያኔ መሮጡንስ ሮጧል። አሁን እየጣረ ያለው ራሱን ተክቶ ለማለፍ ነው። በመሆኑም ካጋጠመው መውደቅ ለመነሳት ማንኛውንም ርምጃ ይወስዳል። ለአብነት ለሃያላን አገራት ራሱን መሸጥ ቀደም ሲል ከፈፀማቸው የነፍስ አድን ርምጃዎች አንዱ ነበር። ከአምስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ሶማሊያ ወስዶ ሲሰዋ አለቆቹ ለስልጣኑ ዋስትና እንዲሰጡት እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም አልነበረም። “ወደድንም ጠላንም አሜሪካኖች ጌቶቻችን ናቸው” የሚለውን አባባል መለስ ዜናዊ በማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች በግልፅ የሚናገረው ነበር። እና አሁንም በጌቶች እርዳታም ቢሆን የኦሮሞን ህዝብ የቁጣ ማእበል ለማፈን ጥረት ማድረግ የማይቀር ነው።
ወያኔ እንደ አጤ ሃይለስላሴ፣ “እንግዲህ ኢትዮጵያን ለመምራት ተራችን ነው ካላችሁ፤ አደራ አገራችሁን ጠብቋት!” ብሎ አልጋውን ለተቃዋሚዎቹ በመተው ከመድረኩ ዘወር ይላል ተብሎ አይጠበቅም። እንደ ደርግ ስርአት፣ “አንድ ጥይት እስኪቀረን እንገድላለን” ቢሉ ግን በትክክል ራሳቸውን ይገልፃቸዋል። የወያኔ ሰዎች እስከተቻላቸው በስልጣን ለመቆየትና በመጨረሻ ራሳቸውን ለመተካት ይጥራሉ እንጂ፤ አገሪቱ የጋራ አገር ናት በሚል እንደ መፍትሄ የሚቀርብላቸውን ለሁሉም ወገን የሚበጅ በጎ ምክር ለመስማት ዝግጁ አይደሉም። ግትርነታቸው ግን መሆን ያለበትን ከመሆን አያስቀረውም። እንደምናየው ህዝባዊ አመፁ ቀጥሎ ከመጨረሻው ጠርዝ ላይ እየደረሰ ነው። እየተስፋፋ አገራዊ መልክ እየያዘ ነው።
የህወሃት ፖለቲካ በማታለል መንገድ ተጉዞ እዚህ ደርሶአል። አዲስ ክረምት ዞሮ በመጣ ቁጥር በምግብ ራስን ስለመቻል መናገር ቋሚ ልማዳቸው ነበር። ሟቹ ሰውዬ “በቀን ሶስት ጊዜ ስለመመገብ” ከመፈላሰም አንስቶ “ትርፍ እህል ለአለም ገበያ በሽያጭ ስለማቅረብ” ጭምር በልበ ሙሉነት ሲገልፅ ደጋግመን ሰምተነው ነበር። ጥቂት የዝናብ መዛባት ሲያጋጥም ግን ለአንድ አመት የሚበቃ መጠባበቂያ ምግብ እንኳ አለመያዛቸው ይጋለጣል። ከአፍሪቃ በውሃ ጎተራነቷ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠች ሃብታም አገር እየመሩ ምግብ መለመን በእውነቱ ማሳፈር ነበረበት። ተለማመዱትና ሳያፍሩ ቀሩ። አየር ባየር የመሬት ንገድ ለመዱና እንደ መንግስት ማድረግ ያለባቸውን ቀዳሚ ስራ ማከናወን ረሱ።
በ2015 ምርጫ 100% የህዝብ ድምፅ እንዳገኙ ለአለም ባወጁ በጥቂት ወራት ልዩነት 100% የኦሮሞ ህዝብ ሲያምፅባቸው፤ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም ከ50% በላይ ሌላው ህዝብ በተመሳሳይ ቅሬታውን ሲገልፅ የህወሃት ሰዎች አልተሳቀቁም። ከመብት ጠያቂው በሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ጀርባ ላይ፣ “የግብፅና የኤርትራ ተላላኪ” የሚል ታርጋ ሲለጥፉ ወለም አላላቸውም። የማያስነቃ ውሸት መደባለቅ በፖለቲካ ውስጥ የተለመደ ሊሆን ይችላል። በተደጋጋሚ ገገማ ውሸት መስማት ግን ያስተክዛል። ከዚህ ሁሉ የተተራመሰና የባከነ ጉዞ በሁዋላ ታዲያ ኢትዮጵያ በህዝባዊ አመፅ ተንጣ መጪ እድሏን ለመተንበይ ያስቸገረች አገር ለመሆን በቅታለች። አሳዛኙ ነገር ህዝቡ በምርጫ ላይ እምነት ማጣቱ ነው። ይህን እምነት ማጣት ለማስተካከል፤ ይህን በምርጫ የማጭበርበርን ልማድ ለማስወገድ እንደገና ሌላ ጊዜና ጉልበት መጠየቁ የማይቀር ነው። በምርጫ ጉዳይ ህዝብን ተስፋ ከማስቆረጥና እምነት ከማሳጣት እንደ ሃይሌ ገብረስላሴ “የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲ አያስፈልገውም” ብለው ቁርጡን ቢናገሩ በተሻለ። ህዝቡም በውሸት ምርጫ ጊዜውን ከማቃጠል፤ በቀጣይ ማድረግ ያለበትን በወሰነ።   
ወቅታዊው ሁኔታ “የኦሮሚያ አመፅ ቀጥሎአል” ከሚለው ዜና “የኢትዮጵያ ህዝብ አመፅ ቀጥሎአል” ወደሚል ደረጃ ማደጉ እየታየ ነው። ከኦሮሞ ህዝብ ያላቋረጠ ተቃውሞ ባሻገር በወልቃይት የተቀሰቀሰው፣ “ትግሬ አይደለንም” ጥያቄ አልተዳፈነም። ባለፉት ጥቂት ቀናት ሰሜን ጎንደር ዳባት ላይ አማራ አማፅያን መንገድ ዘግተው መዋላቸው የአመፁ መስፋፋት ተቀጥያ ነው። ጎጃም ከመሬት መጥበብ ጋር በተያያዘ ቅሬታ አለው። ትናንት የአዲሳባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች “አሸባሪዎች አይደለንም” የሚል ተቃውሞ ይዘው ከስድስት ኪሎ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ በመጓዛቸው ድብደባና እስራት ገጥሟቸዋል። በደቡብ በተለይም ሙርሲ ብሄረሰብ፤ በሃመርና በኦሞ ሸለቆ አካባቢ ህዝብና ፖሊስ መጋጨታቸው ተሰምቷል። ፖሊሶች ልብስ መልበስ ያልጀመሩ ዜጎችን አንገታቸውን እንደ ጉሬዛ በገመድ እያሰሩ ሲያንገላቱ ምስሉ በማህበራዊ ድረገፆች ይፋ ሆኖአል። የግጭቱ መነሻ አሁንም መሬት ነው። በጋምቤላና በቤኒሻንጉልም ተመሳሳይ የአመፅ እንቅስቃሴዎች ቀጥለው ከርመዋል። የሃዲያ ሽማግሌዎች በባህላዊው መንገድ ስብሰባ አድርገው ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ያላቸውን ወገናዊነት መግለፃቸው ባለፈው ሳምንት ከተሰሙ ትኩረት ሳቢ ዜናዎች መካከል አንዱ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደቡብና የኦሮሚያ ህዝቦች መቀራረብ እየጠነከረ መሄዱ የመጪውን ዘመን የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ የሚጠቁም ነው። እንዲህ ያለ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መቀራረብ በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች መካከል ቀደም ብሎ ቢጀመር ኖሮ የመከራው ዘመን ገና ድሮ ባበቃ ነበር።
የአዲስአበባ ታክሲዎች የአንድ ቀን የስራ ማቆም አድማም የወያኔን ደም ስር የነካ ክስተት ሆኖ አልፎአል። በር ከፋች ምልክት ነው። መሞከሪያ ነበር። የትልቁ ምስል ማሳያ ነበር። በትክክልም ውጤቱ ታይቷል። ወያኔ ያለ ልማዱ ለታክሲ አሽከርካሪዎች ጥያቄ 24 ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠቱ በኦሮሚያ የተጀመረው አመፅ ወደ ሌሎች ክልሎችም እንዳይስፋፋ መስጋቱን ይጠቁማል። የህወሃት ደጋፊ ነጋዴዎች ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ እጃቸውን እየሰበሰቡ አዲስአበባ ተከማችተዋል። ገንዘባቸውን ወደ ውጭ ምንዛሪ በመለወጥ ስራ መጠመዳቸውም የከረመ ወሬ ነበር። ይህ ሂደት አላቋረጠም። አላሙዲ በተመሳሳይ የጥቃት ኢላማ ሆኖአል። የቦረና የከብት እርባታው ላይ ከደረሰ አደጋ በሁዋላ ይህን እየፃፍኩ ሳለ እንኳ የጎሞሮ የሻይ እርሻው ላይ ተመሳሳይ የእሳት አደጋ ደርሶበታል።
የትግራይ ህዝብ ይህ ጊዜ እንደሚመጣ ቀድሞ ተንብዮአል። መስፍን ወልደማርያም በትክክል እንደገለፁት የህወሃት ዘራፊዎች መቐለ ላይ የገነቧቸውን ቪላዎች ህዝቡ “የአፓርታይድ መንደር” ብሎ ሲሰይም “እኔ የለሁበትም” እያለ ነበር። ከደሙ ንፁህ መሆኑን እያወጀ ነበር። በአማርኛ ቋንቋ የልጆች ተረት ውስጥ አንድ የማይረሳኝ ድንቅ ታሪክ አለ። አንድ ጅብ ከሁለት ልጆቹ ጋር ተባብሮ አህያ ይጥላል። ከዚያም ልጆቹን አባሮ ብቻውን ይበላል። ሊነጋ ሲል የአህያው ባለቤት ጦር ይዞ መጣ። ልጆቹ ጥለውት ሲሸሹ አባት፣ “አድነኝ ልጄ መዝሩጥ?” ሲል ተጣራ። ልጁም፣ “አባቴ ሆይ! እንደበላህ እሩጥ” ሲል ምላሽ ሰጠ። ይህ ተረት ለህወሃት ደጋፊ ሙሰኞች ጥሩ ምሳሌ ነው። የትግራይ ህዝብ በስሙ በሚነግዱ ጥቂት ከበርቴዎች ምክንያት ሊወገዝም ሆነ ሊወቀስ አይችልም። ትግራይ ላይ ተገነቡ የሚባሉ መንገዶችና ጥቂት ፋብሪካዎች ከሚገባው በላይ አይደሉም። ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ካለ በመላ ኢትዮጵያ ከዚያም በላይ ማድረግ በተቻለ።
በኢትዮጵያ ላጋጠመው የአስር ሚሊዮን ህዝብ የረሃብ አደጋ እርዳታ ለመስጠት በብዛት ወደ አዲስአበባ እየገቡ ያሉት አሜሪካኖች ከፊል አላማቸው ሌላ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለ። ርግጥ ነው፤ የወያኔ ስርአት የሚፈርስ ከሆነ አሜሪካኖች ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ከወዲሁ ሰዎቻቸውን ልከው ሁኔታውን ማጥናት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ወያኔ በአሜሪካኖች በኩል ድርድር ለማድረግ ሽማግሌ መመልመላቸው ወቅታዊ ነው። የህወሃት አመራር በስልጣን ላይ ሳለ ለፈፀመው ወንጀል በማይጠየቅበት መንገድ፤ የደጋፊዎቹ ሃብትና ንብረት በማይነካበት መንገድ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ከተስማሙ ኮርተው ያዋጣቸዋል። አሜሪካኖችም ከደከመው ጋር ከሚዳከሙ ከታጣቂም ሆነ ከባዶ እጅ ተቃዋሚዎች፣ እንዲሁም በስደት ከሚገኙ ታዋቂ ግለሰቦች አዛንቀው አንድ ጊዜያዊ መንግስት ለማቋቋም ከቻሉ ለወያኔም ቢሆን ምንም አይላቸው። በመጨረሻ ከማይቀርላቸው ተገፍቶ መውደቅ ይሻላቸዋል። ሙሰኛ ደጋፊዎቻቸውን ከበቀል ዱላ ማዳን ይቻላቸዋል። በርግጥ እንዲህ ያሉ ወጎች ጊዜው ደርሶ ሰበር ዜና እስኪሆኑ ሹክሹክታ ሆነው ይቆያሉ።
ከዚሁ ሹክሹክታ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ኮምፕዩተሮች የመዘረፋቸው ክስተት አቅጣጫ ጠቋሚ ነው። ኮምፕዩተሮቹን የዘረፉት ያለምንም ጥርጣሬ የጌታቸው አሰፋ ልጆች እንጂ ተራ ሌቦች ሊሆኑ አይችሉም። ተራ ሌባ ፌዴሬሽን ምክርቤት ገብቶ ኮምፕዩተሮችን የመስረቅ ችሎታ ሊኖረው አይችልም። እንዲህ ያለ ድርጊት ከዚህ ቀደምም ተፈፅሞ ነበር። “ጥረት” የተባለው በሙስና የሚታማ የብአዴን የንግድ ድርጅት ምስጢሮቹን ለመደበቅ የሂሳብ ክፍሉን በእሳት አጋይቷል። ከብሄራዊ ባንክ የተሰረቀው ወርቅ እና የሼኽ መሃመድ አልአሙዲ ንብረት ጉዳይም እንዲሁ ምላሽ ያላገኙ እንቆቅልሽ ናቸው። በአሰራር ደረጃ የደህንነት መስሪያቤቱ በህጋዊ መንገድ ማግኘት የሚያስቸግረውን ሰነድም ሆነ ንብረት በሌቦች የማስመንተፍ ልምድ እንዳለው የሚታወቅ ነው። ለአብነት በክንፈ ገብረመድህን የደህንነት ስልጣን ዘመን የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን የእጅ ቦርሳ በሌባ ማስነጠቃቸው የሚታወስ ነው። የመለስ ዜናዊን አስከሬን ጄኔራል ሳሞራ በሄሊኮፕተር አድዋ አድርሶ ሲያበቃ፤ አዲስአበባ ላይ ባዶ ሳጥን መቅበራቸው የአንድ ሰሞን ሹክሹክታ ሆኖ አልፎአል። ይህ በርግጥ ያስቃል እንጂ አያናድድም። ለአዲስአበባ የመለስ ራእይ እንጂ አስከሬኑ ምንም አያደርግላት። የፌዴሬሽን ምክርቤቱ ኮምፕዩተሮች ስርቆት ጉዳይ በተመሳሳይ አላማ ያለው መሆኑን የአካባቢው ሹክሹክታ ይጠቁማል።
ከፀጥታው መስሪያ ቤት ቀጥሎ ወያኔ ሊደብቃቸው የሚፈልጋቸው ሰነዶች የሚገኙት በካሳ ተክለብርሃን ስር በሚገኘው የፌዴሬሽን ምክርቤት ኮምፕዩተሮች ውስጥ ነው። በህዝብ ብዛት መጠን የሚሰፈረው የክልሎች በጀት ጉዳይ፣ የክልሎች ድንበርና የክልሎች ካርታ ጉዳይ፣ የብሄረሰቦች አቤቱታዎች፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይና ውሳኔዎች ሁሉ ወደዚሁ ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት ሲጎርፉና ሲከማቹ ኖረዋል። የወያኔ አመራር ስርአታቸው እንደሚፈርስ ካወቁ በቅድሚያ ማስወገድ ያለባቸው በዚህ ቢሮ ውስጥ የተከማቸውን ሰነድ መሆኑ ግልፅ ነበር። አድርገውት ከሆነ ጥሩ ዘይደዋል።
በጥቅሉ ላለፉት አራት ወራት የተካሄደውን ህዝባዊ አመፅ መታዘብ እንደሚቻለው የቄሮ ወጣቶች ሞትን ንቀውታል። የፍርሃቱን ዘመን ተሻግረውታል። የዝምታውን የብረት በር በርግደውታል። የፖለቲካ ቁማሩን ተረድተውታል። ብዛትና ብርታታቸው ከሚታወቀው በላይ በመሆኑ ጉዳዩ የነብር ጭራ ላይ እንደተተረተው አይነት እየሆነ ነው። Dances with Wolves በተሰኘው የKevin Costner ዝነኛ ፊልም ላይ እንዳየነው ትረካ የቄሮ አመጣጥ ልክ እንደ ከዋክብት ነው። ማለትም ብልጭታዎች ጥቁሩን ሰማይ ሸፍነውታል። የከዋክብቱን ብርሃን ከጥቁሩ ሰማይ ላይ ማስወገድ የሚቻል አይደለም።  የበረዶው ወቅት አልፎ ፀሃይ ስትወጣ የሞቱ መስለው የነበሩ እፅዋትና አዝርእት ምድሩን እንደሚያለብሱት አይነት ናቸው። በሌላ አገላለፅ ከጊቤ ወንዝ ዳርቻ አንድ የተኛ አዞ አለ። አዞው ውሃ ልትጠጣ የመጣችውን ሚዳቋ ቀጨም ከማድረጉ በፊት ህይወት ያለው አይመስልም ነበር። የኦሮሚያ አመፅ እንዲያ ሆኖአል። የኦሮሞ ህዝብ ወደ መጨረሻ ግቡ እየተጓዘ ነው። እንደ ግመል በጥንካሬ ወደፊት እየገፋ ነው። ይህን ለመረዳት የፖለቲካ አዋቂ ወይም ኦሮሞ መሆን ግድ አይደለም።
በመጨረሻ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በቅርቡ “Ethiopia at the Eleventh Hour of Peaceful Change” በሚል ርእስ ካስነበበው ቀንጭቤ ላብቃ፣  
“…በሁኔታዎች ግራ ለተጋቡት አንዳንድ የህወሃት ደጋፊዎች ስለአዲሱ ክስተት ላስታውሳቸው እወዳለሁ። በመጨረሻ የኦሮሞ ህዝብ ፍርሃትን ማስወገድ ችሎአል። ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳሳየን ፍርሃቱን ያሸነፈ ህዝብን ማቆም አይቻልም። with the added fact that the recovery of courage is a contagious phenomenon. Such a movement can be temporarily blocked, ነገር ግን ጨርሶ ማዳፈን አይቻልም።”

የቅዳሜ ማስታወሻ   Gadaa Ghebreab  ttgebreab@gmail.com  www.tgindex.blogspot.com   March 10 2016

3 comments:

Anonymous said...

Nice article. I have one questio, though.
Why do you block people from commenting on your facebook posts?

Tech with Estif said...

Thank You...."THE BLACK SOIL OF ADHA"!!

Anonymous said...

I enjoy the writings of Tesfaye. His mastery of the amharic language is second to none and I am sure the ruling regiem in ethiopis is intimidated by his pen.