Wednesday, February 17, 2016

የበዕውቀቱ ስዩም ወጎች

          በዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” በሚል ርእስ ያሳተመውን መፅሃፍ አነበብኩት። እንደተለመደው ጥሩ ተራኪ ነው። በዚህ ባዲሱ መፅሃፉ በዕውቀቱ ስለማንነቱ ያሰፈረው አዲስ መረጃ ግን ቀደምት ስራዎቹን ወደ ሁዋላ ተመልሼ እንዳገላብጥ አስገድዶኛል። በዕውቀቱ ባለተሰጥኦ ነው። ተፈጥሮ ብእረኛነትን ያለስስት ያስታቀፈችው ድንቅ የዘመናችን ገጣሚ ነው። በተለይ በአጫጭር ስነግጥሞቹ የሚያነሳቸው ጭብጦች አስደማሚ ስለመሆናቸው ብዙ ተነግሮለታል። ለአብነት ሙስናን በአምስት መስመሮች ብቻ የገለፀበት መንገድ የቅኔ ችሎታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፣

እልፍ ከሲታዎች - ቀጥነው የሞገጉ
“ስጋችን የት ሄደ?” - ብለው ሲፈልጉ
በየሸንተረሩ - በየጥጋጥጉ
አስሰው አስሰው - በምድር በሰማይ
አገኙት ቦርጭ ሆኖ - በአንድ ሰው ገላ ላይ

የእነዚህ ስንኞች ገጣሚ እኔ ብሆን ኖሮ ፑሽኪንን እንቀው ነበር። በዕውቀቱ በእነዚህ ስንኞች ከህዝብ የዘረፉትን በቢሊዮን የሚገመት ዶላር ባንክ ውስጥ ስለደበቁ ባለስልጣኖች በቀላል መንገድ ነበር የነገረን። በዕውቀቱ ድፍረቱ የበረታ ነው። ገጣሚነቱ ቃላት አሳክቶ ቤት መምታቱ አይደለም። ነባር አስተሳሰቦችን የመሞገትና በተለየ መንገድ የማየት ልዩ ችሎታ አለው። በተለይም በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ኢአማኒ መሆኑ ሃይል ሆኖ ሳያግዘው አልቀረም። “ከአሜን ባሻገር” ላይ እንደነገረን ለፈጣሪ ከመስገድ የተላቀቀው ሲግመንድ ፍሮይድን ካነበበ በሁዋላ ነው። ሆኖም የአክራሪ ህብረተሰብ ባልደረባ መሆኑን በመዘንጋቱ ዋጋ ከፍሎበታል። የመፅሃፍ ቅዱስን ትረካዎች እያነሳ ከሚተርብባቸው ግጥሞቹ መካከል “ዳዊትና ጎልያድ” ይጠቀሳል።

እግዜርና ዳዊት - አብረው ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ - ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ተገዶ - ለሽንፈት ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል - እንኳንስ በጠጠር

ተቀባይነት አጊኝተው የቆዩ እምነቶችን ገልብጦ በማሳየት ረገድ በዕውቀቱ የተሳካለት ገጣሚ ነው። “ትንሹ ዳዊት ግዙፉን ጎልያድ አሸነፈው” ብለን እናምን ነበር። ከዳዊት ጀርባ ተሸሽጎ ጎልያድን የገነደሰውን አምላክ በፍልሚያው ውስጥ በማስገባት ነባር እምነታችን ላይ ጥያቄ ምልክት እንድናስቀምጥ ያደርገናል። ቀላል አቅም አይደለም። ሌሎች ብእረኞችም በእየሱስ ታሪክ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ካህሊል ጊብራን ለይሁዳ ወገናዊ ሆኖ ፅፏል። እየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ በምናውቀው መንገድ እንዲሞት ተወስኖ ከነበረ፣ ይሁዳ አሳልፎ እንዲሰጠው ተወስኖ ከነበረ ለምንድነው ይሁዳን አንደከሃዲ የምንቆጥረው? በዕውቀቱ እንዲህ ያሉ ተገላቢጦሽ እውነቶችን በኮሚክ አቀራረብ በመተረክ ረገድ የተሳካለት ገጣሚ ነው። ለአብነት ዲዮጋንን የተቸባቸው ስንኞች አስደማሚ ናቸው።

ውሻው ዲዮጋንን - እዩት ተጃጅሎ
በከንቱ ይጮሃል - “ሰው የት አለ?” ብሎ
ሰው ሰራሹን ፀሃይ - በጣቱ አንጠልጥሎ

በዕውቀቱ “ከአሜን ባሻገር” የሚል መፅሃፍ ፅፎ እስኪያሳትም ድረስ የጎጃም አማራ ይመስለኝ ነበር። “ስምና ማንነት” የምትለውን ምእራፍ ሳነብ ግን በዕውቀቱ መሰረቱ ኦሮሞ መሆኑን አወቅሁ። በመግቢያዬ እንደገለፅኩት የዚህን ወጣት ገጣሚ ስራዎች መለስ ብዬ ለማየት የተገደድኩት ከዚሁ ማንነቱ ጋር በተያያዘ ግጥሞቹን ለመመርመር ነበር። በርግጥም ከዚህ ቀደም ትርጉም አጥቼላቸው ለነበሩ ከጥቂት በላይ ስንኞቹ አሁን ምክንያት አገኘሁላቸው። ወደ ግጥሞቹ ከመግባቴ በፊት ግን በዕውቀቱ ስለማንነቱ የገለፀውን ባጭሩ ልጠቃቅስ።

አያቱ አቶ በዳዳ ይባላሉ። ጅባት እና መጫ (አምቦ) ተወልደው ጋርዱላ የተባለ አካባቢ ኖረዋል። አያቱ ጥቂት ልጆች ወልደው ሲሞቱ አባቱንና ወንድሞቹን የማሳደግ እጣ እናቱ ቀደም ሲል ከሌላ ከወለዱት ወንድማቸው እጅ ላይ ወደቀ። የአያቱ ስም የተቀየረው በዚህ ጊዜ ነበር። በዕውቀቱ ይህን ሁኔታ ሲገልፅ፣

“አባቴ በመጀመሪያ አባቱን አጣ። ቀጥሎ የአባቱን ስም አጣ።” ሲል አስፍሮአል።

በዕውቀቱ ስለ ዘር ጉዳይ አንስቶ በመፅሃፉ ከማካተቱ በፊት ከራሱ ጋር ጥቂት ሳይሟገት አልቀረም። አጎቱ አቶ አማረ፣ “ስለዘርና ስለሃይማኖት በመፃፍና በመከራከር ጊዜህን አታጥፋ” ብሎ ቢመክረውም ምክሩን ባለመቀበል ይህንን ምእራፍ ለመፃፍ እንደበቃ አስፍሮአል።

አባቱ አቶ ስዩም “በዳዳ” የሚለውን የአባታቸውን ስም ለመቀየር ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ለበዕውቀቱ ነግረውታል። የአሳዳጊ ግማሽ ወንድማቸውን ፍላጎት መጋፋት ግን አልቻሉም። በርግጥ “በዳዳ” የሚለው ቃል በኦሮምኛ ትርጉሙ፣ “የበለፀገ ወይም ሃብታም” ማለት ነው። ይህ ቃል ግን በአጋጣሚ በአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ብልግና ተብለው ከተመዘገቡ ቃላት ጋር ይቀራረባል። ስለዚህ ይህንን ስም ይዞ አማሮች ወደ በዙበት ትምህርት ቤት መሄድ የሚያደርሰውን ጉዳት የአቶ ስዩም አሳዳጊ ተገንዝበውት ሊሆን ይችላል። በዕውቀቱ ግን በዚህ አይስማማም። ጉዳዩን ቀለል አድርጎ “ህያውነት ነው” ይለዋል። በዕውቀቱ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ መጠራት እንደሚፈልግ ከፅሁፎቹ ተረድቻለሁ። ለነገሩ በመፅሃፉ የአያቱን ጉዳይ ማንሳቱ በአስረጅነት እንጂ ስለዘር ጉዳይ ለመነጋገር አይደለም።

በዕውቀቱ የአያቱ ስም “ከበዳዳ ወደ መሰለ” የተለወጠበትን ምክንያት ለማወቅ ጥቂት ጉዞዎችን አድርጎአል። “በዳዳ የሚለው ስም ከአባቴ አባትነት ለምን እንዲቀየር ተፈለገ? በዘመኑ የፖለቲካ ጫና ወይስ በህያውነት” ሲል ቢጠይቅም ለዚህ ጥያቄ ግን ምላሽ አያገኝም። አዲሳባ ኗሪ የሆነ አማረ የተባለ አጎቱ ስቆ ብቻ ዝም አለው። የአጎቱ ስቆ ዝምታ በዘር ፖለቲካ ላይ ለመነጋገር ባለመፈለግ ይመስላል። አጎቱ፣ “ሰዎች በውይይት የሚግባቡበበት ዘመን እስኪመጣ አርፈህ ግጥምህን ፃፍ” ሲል ይመክረዋል።

በዕውቀቱ ግን የአጎቱን ምክር አልሰማም። በዳዳ የሚለው የአያቱ ስም ለምን እንደተቀየረ ለማወቅ ፍለጋውን ቀጠለ። ስም ቀያሪ ትልቅ አጎቱን ለመጠየቅ እስከ አለታ ወንዶ ቢጓዝም ምክንያቱን አልነገሩትም። በመቀጠል አባቱን ለመጠየቅ መንኩሳ ሄደ። አባቱ ግን ሸፋፈኑበት። ዝምታን መረጡ። በዕውቀቱ አልተዋቸውም። በዳዳን ትቶ መሰለ የሚለውን ስም ይዞ አባይን መሻገሩ ለተቀባይነቱ ጠቅሞት እንደሆን በቀጥታ አባቱን ጠየቀ። አባቱ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ውጥረቱን ለማርገብ አክስቱ ጣልቃ ገብታ ተቆጣች። ኦሮሞ በጎጃም የተከበረ መኳንንት መሆኑን ተናግራ ጉዳዩን ቋጨችው። በመግቢያዬ እንደገለፅኩት የበዕውቀቱ ሽሽግ ማንነት በቀደምት ስነግጥሞቹ ውስጥ ተንፀባርቀው እንደሆን ለማየት መለስ ብዬ ስራዎቹን ፈታትሼ ነበር። ከምስጢራዊ ስንኞቹ መካከል ጥቂት አገኘሁ፣

በነፍሴ ሰማይ ላይ
ቢሰርቅ ጣምራ ፀሃይ
አንዱን ጋርጃለሁ
ሌላው ደምቆ እንዲታይ

“ምን ማለቱ ነው?” ብዬ ሳስብ “የአቶ በዳዳን ኦሮሞነት ሸሽጎ አያቱ ባልሆነ ስም እየተጠራ መቀጠሉን እየተቃወመ ይመስላል” አልኩ። “አንዱን ጋርጃለሁ - ሌላው ደምቆ እንዲታይ” የሚለው ኦሮሞነቴን ደብቄ ሌላ መስዬ እየታየሁ ነው የሚል ትርጉም የያዘ መሰለኝ። እንግዲህ እኔ እንደገባኝ ነው። በእውቀቱ ቢጠየቅ ግጥሞቹን የቋጠረበትን ሌላ ምክንያት ሊሰጥ ይችላል። ስለዚህ የኔን አስተያየት ስታነቡ የአንባቢ መብቴን ተጠቅሜ እንጂ የበዕውቀቱ ልብና አንጎል ውስጥ ገብቼ ያሰበውን ለማወቅ እንደማልችል ከወዲሁ ላሰምርበት እፈልጋለሁ። በዕውቀቱ በዚህ አላበቃም፣

ቀንድ አውጣ ሆይ!
ውብ ዛጎልህ አማለለኝ
ከጎጆህ ላስወጣህ ነው (ይቅር በለኝ)
‘በዝግ አለም - ሰማይ ጣራ ነው’ ይባላል
ያለውበት ነውንጂ - ያለቤት መኖር ይቻላል

እነዚህ ስንኞች ለኔ የሰጡኝ ትርጉም፣ በዕውቀቱ አቶ በዳዳን ከተሸሸጉበት ዛጎል ጎትቶ ለማውጣት መወሰኑን ነበር። በርግጥም እንደፎከረው ፈፅሞታል። ያለ ውበት መኖር እንደሚቻል ለማሳየት ሞክሮአል። አያቱ በዳዳ መሆናቸውን ሲገልፅ በከበበው ማህበረሰብ አመለካከት ውበቱ እንደሚቀንስ የግድ ያውቃል። ከዚህ በሁዋላ ሌሎች ወገኖች በዕውቀቱ ባለበት ስለ ኦሮሞ ለማንሳት ቃላት መምረጥ ሊኖርባቸው ነው። በዕውቀቱ አያቱን ከተሸሸጉበት አውጥቶ ለነፃነት ከማብቃቱ በፊት በዚሁ ቁጭት የፃፋቸው የሚመስሉ ስንኞችን ማስተዋል ችዬ ነበር። ለአብነት በአንድ ግጥሙ ኦሮሞ - አማራንና ትግሬን በገፀባህርይነት ያመጣና እንዲህ ሲል ያላግጣል፣

በታሪክ ሜዳ ላይ
አሉላ ጎበና
ወንዱን አስከትለው - ሲገድሉ ሲሞቱ
አባ ገብረሃና
እርስዎ ባይኖሩ - ምን ይውጠው ሴቱ?
ጨመረልኹ መሰል - ባባ ነፍሶ ፈንታ
እንደ አንደበትዎ - እንትንዎ መንታ
አንዱ ለቀን ሲሆን - አንደኛው ለማታ

“ባባ ነፍሶ ፈንታ” ማለቱ ባልቻ አባነፍሶ ስልብ ነበሩ ስለሚባል ሲሆን፤ “እንትንዎ መንታ” ማለቱ ደግሞ አለቃ ገብረሃናን እንደ ምላስዎ መሾል (የቀጣፊነት ችሎታ) ሁለት ብልት ይዘዋል ማለቱ ነው። ሌሎች ጦር ሜዳ ሲሞቱ እርስዎ ውሎና አዳርዎ ከሴት ጋር መዳራት ነው ማለቱ ነው። በዕውቀቱ እንዲህ በመረረ ሁኔታ ሊሳለቅ የቻለው ምን ተሰምቶት እንደሆን ባውቅ በጣም ደስ ባለኝ ነበር። በተለይ ገዢዎች ላይ ቅሬታና ቂም እየያዘ እንደመጣ የሚጠቁሙ ከጥቂት በላይ ስንኞቹን ታዝቤያለሁ። አንዷ እንዲህ ትላለች፣

አልወጣም ተራራ - ደመናውን ላብስ
ቀስተደመናውን - ሽቅብ ልቀለብስ
አልዋስም እኔ - ካቡነ ተክሌ ክንፍ -ከያ’ቆብ መሰላል
እኔ መውጣት ሳስብ - ሰማዩ ዝቅ ይላል

ዝቅ ይላል ያለው ሰማይ ስልጣን ነው። የትኛው ስልጣን እንደሆነ ግን አልገባኝም። የወያኔን ማለቱ ይሆን? ወይስ የወደቀውን የፊውዳል ስርአት አመለካከት? በእውነቱ አልገባኝም። ቁልቁል ይቀለበሳል ያለው ቀስተደመና ግን የኢትዮጵያ ባንዴራ ነው። የአቡነ ተክሌ ክንፍና የያእቆብ መሰላል ያላቸው ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ሊሆን ይችላል። በዕውቀቱ ከሁሉም ለይቶ ተክልዬ ላይ መቀለድ ይወዳል። ምክንያቱን አላውቅም። በዚህ ግጥሙ ግን በባንዴራው፣ በቤተክርስትያን እና ከፍ ባለው የአመለካከት ስልጣን ላይ ርግማኑን ያወረደ ይመስላል። ርግጥ ነው፤ ስነግጥሞች ብዙውን ጊዜ ለትርጉም ክፍት ስለሆኑ አንባቢ በራሱ መንገድ የመረዳት መብት አለው።

የበዕውቀቱ ቀደምት ግጥሞች “ከአሜን ባሻገር” ላይ ከተጠቀሱት አቶ በዳዳ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማየት ሞክሬያለሁ። በዕውቀቱ የመፅሃፉን ርእስ ለምን “ከአሜን ባሻገር” ሲል እንደሰየመው ምስጢር አልነበረም። በቀጥታ ከአያቱ ከአቶ በዳዳ ጋር ይያያዛል። እሱም በዚያው ምእራፍ ላይ እንዲህ ሲል ገልፆ ነበር፣

“የተለያዩ ባህሎችን በአንድ በገና ውስጥ እንደተወጠሩ አውታሮች ማስተናገድ በማይታወቅበት ጥንታዊ ማህበረሰብ ውስጥ ግለሰቦች የገናና ባህሎችን ምልክት አሜን ብለው ከመቀበል ያለፈ ምርጫ አልነበራቸውም።”
እና “ሉአላዊነት” የሚል ግጥሙ ብሶት ያዘለ ነበር፣

የጋራችን አለም - የጋራችን ሰማይ
የብቻችን ህመም - የብቻችን ስቃይ

ደመናው እንዴት ይታይ
ሸፍኖት ሰንደቅ አላማው
ሸፍኖት ብሄራዊ መዝሙሩ
ብሄራዊ ልቅሶውን ማን ይስማው?

ከእናቴ፣ ከአባቴ፣ ከወንድም ከእህቴ
ከወዳጅ ጠላቴ
የእንባ ጡብ ሰብስቤ
ሽቅብ ደራርቤ
የሰራሁት ህንፃ - መቸም አልፈረሰ
ሚፈርስም አይመስለኝ - ምፅአት ካልደረሰ

“ከአሜን ባሻገር”ን ሳነብ ገጣሚው ውስጡ የሚቃጠል ባህር ሆኖ ተሰማኝ። ባህሩ የእንባ ጥርቅም መሆኑን ራሱ ነው የነገረን። ምን ቢሆን ነው በዕውቀቱ ልቡ ውስጥ የእንባ ኩሬ ያጠራቀመው? ምንድነው ከውስጡ የሚጮኸው? ምንድነው በቀጥታ መናገር ያልቻለው? በአንድ ሰማይ - በአንድ አገር ስር ዜጎች አብረው እየኖሩ፤ ላንደኛው ወገን ስቃይ እንደሆነበት ሲነግረን አልገባ ብሎን ይሆን? የኦሮሞ ህዝብ ላይ ሚዛን ያጣ ወቀሳ ከሚያዥጎደጉዱ ሰዎች መሃል ተቀምጦ የውሸት ሳቅ መሳቅ ሰልችቶት ይሆን ማንነቱን ይፋ ለማድረግ የተገደደው? የትልቅ አጎቱና የአባቱ ዝምታ አስጨንቆት ይሆን የሚከተለውን ግጥም የፃፈው?

አዳኝ በንስሃ - ሰይፉ አልዶለዶመም
ታዳኝ በፀሎቱ - ካራጆች አልዳነም
ተኳሹ ቢዋልል - አልመታ ቢል ተኩሱ
ካፈሙዝ ይጠጋል - ኢላማው እራሱ

“ከአሜን ባሻገር” ላይ በዕውቀቱ ልጅነቱን በተመለከተ ጥቂት ያነሳል።
“…ከተወለድኩበት ቤት ግርጌ የሚንቆረቆረው፤ ቀይ አቧራዬን ከእግሬ ላይ ያስለቀቅሁበትን ደቦሆላ የተባለው ወንዝ የአማርኛም ሆነ የግእዝ ትርጉም እንዳለው ለማረጋገጥ ሞክሬ አልተሳካልኝም። ለካ ደቦሆላ በኦሮምኛ Daboolaa (የተከደነ) ማለት ኖሮአል?...” ሲል አስፍሮአል።

የበዕውቀቱ የትውልድ መንደር መንኩሳ ትባላለች። መንኩሳ ራሱ ቃሉ ኦሮምኛ መሆኑን አልደረሰበትም መሰለኝ አላነሳውም። “መና” ማለት “ቤት” ማለት ነው። “ኩሳ” ደግሞ “ማከማቻ” ነው። “ማከማቻ ቤት” ወይም “መጋዘን” እንደ ማለት ነው።

በዕውቀቱ በመፅሃፉ አንዳንድ ታሪካዊ ሁኔታዎችን እያነሳ ለመሞገት ሞክሮአል። አብዛኛው ጥናታዊ እና የታሪክ ትንተና ጉዳይ ነው። ፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን እና ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ስለ ኦሮሞ የሰሩትን የተከበሩ ስራዎች እያጥላላ፣ ‘ይሄ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እገሌ የተባለው ፈረንጅ በመፅሃፉ ይጠቅሰው ነበር’ ብሎ ሊሞግት ይሞክራል። ይህን መሰል ሙግት መቸም ፈረንጅ የፃፈውን የበለጠ የሚታመን ማመሳከሪያ የማድረግ የአበሻ ፀሃፊያን ልማድ ሆኖአል። የባለታሪኩ ማስታወሻ በእጅ እያለ አንድ ፈረንጅ ከአስጎብኚው የሰማውን የበለጠ ማመን ያስተክዛል።

በዕውቀቱ አጤ ምኒልክ የፈፀሙትን በጎም ሆነ ክፉ ተግባር ከጊዜው ጋር እንዲታይ፣ እርሳቸው የፈፀሙትን ሌሎችም የወቅቱ ነገስታትና መሪዎች እንደፈፀሙት ለማሳየት መሞከሩ በርግጥ ለአብሮ መኖር የሚበጅ በመሆኑ ተገቢ ነው። ‘የአኖሌ የጡት ቆረጣ ታሪክ እውነት አይደለም’ ሲል ማስተባበሉ ግን መረጃ የለውም። እንደተለመደው ‘ጡት ተቆርጦ ቢሆን ኖሮ እገሌ ይፅፈው ነበር።’ አይነት ክርክር ነው። የፕሮፌሰር መሃመድ አባስን መፅሃፍ እንኳ ያነበበ አይመስለኝም። “የቡርቃ ዝምታ” ታሪክ ቀመስ ልቦለድ እንደመሆኑ ገፀባህርያት የሚናገሩትን እንደ ደራሲው አቋም መውሰድ ልክ አለመሆኑን በዕውቀቱ አያጣውም። መቸም ችግር ነው፤ የከበበውን ስሜታዊ ማህበረሰብ ለማስደሰት ያደረገው ይሆናል።

“የጁገል ልባዊ ወግ” በሚል ርእስ የፃፍኩትን ትረካም በዕውቀቱ ይጠራጠረዋል። ለማረጋገጥ ግን ቀላል ነው። ጁገል ሄጄ ያነጋገርኳቸው እናት አመቱላ ሻሽ አቦኝ ሞተው ከሆነ ዘመዶቻቸው ይኖራሉ። የሃረሪ አዛውንቶች ታሪካቸውን ሲናገሩ ከአንድ ምንጭ እንደሚቀዳ ውሃ ይዘቱ አንድ ነው። የሃረሪ የታሪክ አባት ብዬ የጠቀስኩት አብዱሰመድ እድሪስ ተራ ሰው አይደለም። በዕውቀቱ ሊያናንቀው ሞክሯል። ስለማያውቀው ነውና አልፈርድበትም።

ይልቁን በእውቀቱ ስለ ጎጃም ነባር ጌቶች የተረከው ተነባቢ ነው። የጎጃም መስራች አባት ኢቢዶ የሚባል የቦረና ኦሮሞዎች መሆናቸውን የተሻለ ምንጭ አጣቅሶ ተንትኖአል። ኢቢዶ ከወለጋ ከብት እየነዳ ወደ ጎጃም ከገባ በሁዋላ ለጎጃም ስርወ መንግስት መሰረት መጣሉን ያብራራል። በዕውቀቱ በትረካው ደጃዝማች ጎሹ ኦሮሞ መሆናቸውን ጠቅሶ ሲያበቃ፤ የጎሹ ልጆች ኤሌምቱ፣ ዶሪ፣ ተሰማ ይባሉ እንደነበር ይገልፃል። ሁዋላ ንጉስ ተክለሃይማኖት የተባሉት እንግዲህ የተሰማ ጎሹ ልጅ ‘አዳል ተሰማ’ ናቸው። ኦሮሞ በጎጃም “መኳንንት” የመሆኑ ጉዳይ በሰነዶች የተረጋገጠ መሆኑን አብራርቶአል። በእውቀቱ በትረካው፣ ጎጃም ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎችን በመዘርዘር ግዛቱ በኦሮሞዎች እንደተመሰረተ ያብራራል። ካሰፈራቸው ስሞች መካከልም ባሶ፣ ሊበን፣ ጂጋ፣ ቡሬ፣ ሶማ፣ ዲማ፣ ኢልማና ዴንሳ፣ መጫ ይጠቀሳሉ። ባህርዳር ራሷ መጫ ስር መሆኗን ግን አልጠቀሰም። የበዕውቀቱ ትንተና ዶክተር መረራ ጉዲና “ጎጃም ኦሮሞ ነው” ከሚለው ጋር ይመሳሰላል። በእርግጥ እንዲህ ያለ ወግ ወያኔ ፊት ማውራት ጥሩ አይመስለኝም። ያላሰቡትን ማሳሰብ ይሆናል። “እንኳን ባሩድ ሸቶሽ፤ እንዲያውም ጠርሙስ አረቄ ትጨርሺያለሽ” እንዲሉ እንዳይሆን።

እንግዲህ በዕውቀቱ ስዩም በነገረን አዲስ ማንነቱ መሰረት በተለይ በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የሰላምና የትብብር ወንዝ እንዲፈስ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። ዳር ላይ በመቆም “እገሌ ሊያጋጨን ይህን ፃፈ” እያሉ ሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር ተላቀው እንደ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በር ከፋች ሚና መጫወት የበለጠ ውጤት ያስገኛል። በዕውቀቱ አቡነ ተክልዬን በመተረቡ የደረሰበትን የቡጢ አደጋ በማስታወስ መስጋት ያለበት አይመስለኝም። መቸም በአንክል ሳም አገር ህግ መሰረት በአያት መጠራት ደንብ ስለሆነ “ኢጆሌ በዳዳ” ማለት ቢጀምር፤ የአድናቂዎቹ ቁጥር ከግራም ከቀኝም ይጨመርለታል። ቀልዳዊ ፅሁፎች ቀልቡን ከሚስቡት “ከአሜን ባሻገር” ላይ እንደጀመረው ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ ቢሰራ መንፈሱን የሚያረካው ይመስለኛል።
በመጨረሻ የዘመናችን ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም በቋጠራት አንዲት አስቂኝ ቅኔ ልቋጭ። አስቂኝ እንኳ አይደለችም። እንደ ካራሜላ ጣፋጭ ናት። “ፍካሬ እውነት” በሚል ርእስ የቋጠራት ስትሆን፤ እንዲያው ሳስባት የኢትዮጵያን ሚዛን ያጣ ታሪክ አፃፃፍ ለማሳየት የተቋጠረች የ’ሳትዳር ወግ ትመስለኛለች።

“ሰማዩ!
እንዲህ እንደዛሬው ርቆ ሳይወረወር
ሁሉ ‘ንዳሻው ሚቆርሰው
ሁሉ ‘ንዳሻው የሚጎርሰው
ግዙፍ እንጀራ ነበር”
ብለሽ የነገርሺኝን እውነት ነው ተቀብያለኹ
ምክንያቱም ወድሻለኹ

“አያቴ
ሶስት መቶ አመታት ኖሩ
የመቶ አመት ሰው እያሉ
ብርቱ ፅኑ ነበሩ
ዝሆን በጥፊ ጣሉ
አንድ ጥይት ተኩሰው ሶስት ነብሮች ገደሉ”
ብለሽ የነገርሺኝን እውነት ነው ተቀብያለኹ
ምክንያቱም ወድሻለኹ

“አባቴ
ከሰዎች ሁሉ ይለያል
ባይኖቹ ብቻ ሳይሆን በማጅራቱም ያያል”
ብለሽ የነገርሺኝን እውነት ነው ተቀብያለኹ
ምክንያቱም ወድሻለኹ

ግና ጅል እንዳልመስልሽ አይደለሁም ተላላ
በርግጥ በጄ ብላሻለች ነፍሴ ሁሉን ተቀብላ
እውነት ማለት ከሚወዱት መስማማት‘ንጂ
አይደለምና ሌላ…

Gadaa Ghebreab የቅዳሜ ማስታወሻ www.tgindex.blogspot.com ttgebreab@gmail.com feb 13 2016

 

6 comments:

Tech with Estif said...

Thank you......."THE BLACK SOIL OF ADHA"

Tech with Estif said...

THANK YOU................."THE BLACK SOIL OF ADHA".....

Tech with Estif said...

Thank You...........THE BLACK SOIL OF ADHA....

Anonymous said...

መጽሐፉን አነበብኩት። በርግጥም ጥልቅ፣ደፋርና ወግ ቀመስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እኔን ያስገረመኝ ግን በውቀቱ ምን ያህል በራሱ ላይ የጨከነ፣ የሚመጣውን ፀያፍ የስድብና የውግዘት ወርጅብኝ ለመቀበል ቆዳውን አደንድኖ የቀረበ መሆኑ ነው።

በጭራሽ የመቀራረብ ምልክት የማይታይበትን እንደ ምድር ዋልታ ጫፍና ጫፍ የረገጠውን ጽንፈኛ የብሔረተኝነትና የአሓዳዊነት የፖለቲካ ልፊያ ያለምንም ርኅራሄ የዘነጠለበት አቀራረቡ እስካሁን ከቀረቡት ሠነዶች ሁሉ የተለየ ያደርገዋል።

ኦሮሞ እንዳልተገፋ፣ዝቅ ተደርጎ ሲታይ እንዳልኖረ፣ ለዚህች አገር ህልውና ከማንም በላይ መስዋእትነት ግብሮ መሪነትን፣ እኩል ተሣታፊነትን እንዳላገኘ ተረድቼበታለሁ። ይልቅ ቅር ያለኝ፥ እኔ እንኳን የማውቀው በደቡብ ሕዝቦች ላይ የነበረውን ንቀት ጠገብ አስተሳሰብ ጥቂት መስመርም ቢሆን አለመስጠቱ ነው።

ከዚያ በተረፈ ባንተ መነጽር የታየው አቀራረብ ከኪነጥበብ አንጻር ሲታይ ደስ ይላል፤ ምክንያቱም የዊሊያም ሼክስፒርን “የቬነሱ ነጋዴ” ገጸ ባሕርያት የተላበሰ በመሆኑ።

ባንድ የቅርብ ጽሑፍህ ላይ የተጠቀምከውን የምዕራባውያንን ብሂል ደግሜ ላንሳ፤ ጊዜው የደረሰን ሐሳብ ማዳፈን አይቻልም። (there is nothing as powerful as an idea whose time reach) ሌላው ዓለም ይህንን ተረድቶ ያደጋ ወይም የውድመት መቀነሻ ዘዴ (disaster prevention & management) ከትምህርቱ፣ከቀደመው ልምድ በመውሰድ አደጋውን ከፍ ባለ መጠን ይቀንሰዋል ወይም በመልካም ጎኑ ይጠቀምበታል።

በውቀቱ ያደረገው ይህንኑ ነው። በአሐዳውያንና በብሔረተኞች መካከል ያለው ውጥረታዊ መሳሳብ (centrifugal vs centripetal) የሚፈጥረው መላተም የሚያስከትለው ፍንዳታ የሂሮሺማ ዓይነት መሆኑን ሳይጠራጠሩ መገንዘብ። ከዚህ አደጋ መፈወስ የሚቻለው እንደ በውቀቱ ምሑራዊ ልዕለ ሃሳብ (critical thinking) ቦታውን ሲረከብና የኢንተርኔቱ ዓለም የማይረባ ጫጫታ በሕገ ሣይንስ (logical reasoning) ሲመራ ነው።

ይህን ጽሑፍ በቀጥታ ወደ አንተ የላኩት ካንተ የሚገኘው ጥቅም ብዙ ስለሆነ ነው። ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ላንተ ያላቸውን የመረረ ጥላቻ ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ፀያፍ ቃል ሁሌም ይገርመኛል። እርግጥ እኔንም ወደ ንዴት የሚከቱ አቀራረቦች የሉም ማለት አይደለም፤ ልዩነቱ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ማየት መቻሌ ነው። ደራሲ ነህ በኅሊናህ ጓዳ የሚርመሰመሰውን፣ ከልብህ ምንጭ የሚፈልቀውን ትጽፋለህ ምንም ቢሆን። ጨለማ የማይጠቅም ቢሆን ኖሮ የፎቶግራግ ሣይንስ ምን ይውጠው ነበር?

ኢትዮጵያ አሁን የለበሰችውን ጨለማ እንደ ፎቶግራፉ ሣይንስ ከመዓቱ ውስጥ ምሕረት ማምጣት የሚችል(redeemer) ምሑራዊ ሐብት ካጣች መጀመሪያውኑም ትምህርት አልነበረም ማለት ነው፥ የነበረው ማንበብና መጻፍ፣ ተመረቅና ተመረቀች (ማመተመ) ነበር ማለት ነው። አሁን ያለው እውነታ የሚያሳብቀውም ይህንኑ ነው ባይ ነኝ።

አንተ ግን፥ ወልደ ገብረአብ ተስፋዬ ሆይ፤ ዛሬም፣ ነገም እንደቀደሙት ጊዜያት ሁሉ ጻፍ። በውቀቱ ስዩም የሞገተህ እኮ ስለጻፍክ ነው። ማን ያውቃል እነ ማመተመ አንድ ቀን ብልጭ ብሎ ይበራላቸው ይሆናል። ያን ጊዜ ጨረቃ ያለቀሚሷ ጨለማ አታምርም፥ ብለው ለማስዋብ ይባንኑ ይሆናል።


ሰላም
ተስፋዬ

Unknown said...

Dear Tesfayea , በመጀመሪያ ላንተ ያለኝን አድናቆት ሳልገልጽ አላልፈም አንተም እንደ በዕውቀቱ ተፈጥሮ ያለስስት ብዕሯን የለገሰችክ ሰው ነክ ቀኑን ሙሉ ያንተን ጽሁፎች ሳነብ ብውል አይሰለቸኝም እንደውም ስትጽፍ የምትጠቅሳቸው ቦታዎች ባላውቃቸውም የማውቃቸው ያህል በምናቤ እስላቸዋሉ ግን በኢትዮáያዊነት መነጽር ሳይክ ግን << You are Destructive >> ያንተ ብዕሮች ከጥይት የበለጠ የሰውን ልጅ ይጎዳሉ፣ በ አጭሩ ( You Don’t Want to See unified Ethiopia) የየት ሀገር አንድነት ነው እስኪ ጽጌሬዳ አበባ ተይዞና ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎ የመጣው ? ያንተስ ይሄንን መጻፍ ታሪካዊ ፋይዳውን ወይስ ታሪካዊ ፍዳውን ነው የሚያጎላው ? የኦሮሞ ህዝብን ከ አማርኛ ተናጋሪው ህዝብ ጋር ማቃቃር ማለት ኢትዮá ያ ትጥፋ ማለት ነው፡፡ ደግሞ በጣም የገረምከኝ ለበዕውቀቱ የሰጠኸው ምላሽ ላይ ለምን የሱን ብሄር በመጥቀስና ከበፊት ግጥሞቹ ጋር በማነጻጸር ምላሽ ትሰጣለህ? Anyways ይህ ለኔ የሚያስረዳኝ እንደተሸነፍክ ነው እንጂ እንደዚህ መንደራዊነትና ጎጠኝነት ያለው ምላሽ ከእንደ አንተ አይነቱ ምርጥ ፀሃፊ አይጠበቅም ለማንኛውም ሃይለ ቃል የበዛበት ቃላት ከተጠቀምኩ በጣም ይቅርታ እያልኩ እንደ በዕውቀቱ ስዩም ያሉ ጸሃፊዎች እንዲበዙና እንዳንተ አይነቶቹ ደግሞ ቅን ልቦና እንዲገዙ እያልኩ አበቃለሁ፡፡

doni said...

ኢትዮ..…አማራ

ሰንደቃላማችን ከፍ ሲል ለዓለም
ሰማሁሽ ስትይ ኢትዮጲያዊ ቀለም
በራስሽ ፈጠራ ቀለሙን ቀማሚ
መሰረቱን ንደሽ ጣሪያዉን ልታቆሚ
………………እዉነትን ስታሚ
………………..ቅጥፈትን ስትሰሚ
ደምቆ እንዳይታይ ኢትዮጲያዊ ቀለም
ጦሰኛዋ አንቺ ነሽ ሌላ ምክኒያት የለም
ትግሬ ነዉ ኦሮሞ?
ወላይታ ሲዳሞ?
አፋር ነዉ አደሬ?
በትምከት ፉካሬ
ማነዉ ያመሰዉ አገሬን?
እንዳንቺ አስተምህሮት
አንቺና ኢትዮጲያ ብቸኛ ወዳጂ
ሌላዉ ታዛቢ ነዉ ሊያዉም በግዳጅ
ዜግነት ለማግኘት ያንቺ መመዘኛ
ከቤሔር አማራ ከቋንቋ አማረኛ
ተፈጥሮ ብትከዳሽ ሆነሽ ነጭ ደሃ
ከእንስራሽ ብታጪ የምትጠጭዉ ዉሃ
የታሪክ አሻራ ድንጋዩን ክበሺ
ማንም ሳይደርስብሽ የምትናከሺ
በቅጥፈት ብዕርሽ ከትበሽ ከብራና
የእዉነት ጀንበር ወጥታ ሲገለጥ ገመና
ቀለሙም ተነነ…..……….ታሪኩም ተናደ
……………………………….ሳይቀር ለናሙና
የተካበ ድንጋይ ሲተረክ ለዓለም
ተንዶ አገኘሁት ኢትዮጵያዊ ቀለም
እንደሕዝባችን ፍቅር ጎልቶ እንዳልደመቀ
የትምክህት ምሶሶ በጉራ ወደቀ
አንድነት አይመጣም በከንቱ ፉከራ
ጥላቢስ እያለ ኢትዮ……..…… ተራራ
…………………….ኢትዮ…………... አማራ

ከዶኒ ዳን…የግጥም ማህደር…