Friday, January 16, 2015

ግንቦት 7 እና አርበኞች


የልደት በአል በዋለበት ማለዳ ለመናፈስ ያህል ወደ ጎዳና ሃርነት ብቅ ብዬ ነበር። የማውቀው ሰው አቆመኝና ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ወግ አነሳ። እንዲህ ስል ጠየቀኝ፣   
“የግንቦት 7 እና የአርበኞች ግንባር ሰዎች አስመራ ገብተዋል የሚባለው እውነት ነው?”
“ጊዮርጊስን! አልሰማሁም!”
“ኢንተርኔት ላይ’ኮ ወጥቶአል።”       
“አሃ! ሜዲያ ላይ ወጥቶአል እንዴ?” አልኩ፣ “...እንደሱ ከሆነ ሰምቻለሁ።” 

እየቀለድን ወጋችን ቀጠለ፣

“እስኪ ልጠይቅህ ‘ውህደት’ የሚል ነገር ተፅፎ አንብቤያለሁ። ማን ከማን ጋር ነው እየተዋሃደ ያለው? OLFና ግንቦት 7 ናቸው የሚዋሃዱት?”
“አይመስለኝም። የርስበርስ ውህደት ነው።”
“ምን ማለትህ ነው?”

ቡና ልንጠጣ ካፍቴሪያ ገባንና ወጋችን ቀጠለ። ወዳጄ የፖለቲካ ወግ የሚስበው ቢሆንም ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በቂ መረጃ አልነበረውም። እንዲህ አለኝ፣

“የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ለምንድነው በዘር የሚከፋፈሉት? በአንድ አገር ውስጥ አብረው መኖራቸው ካልቀረ ለምን በኢትዮጵያዊነት አንድ ሆነው አይደራጁም? በዘርና በጎሳ መደራጀታቸው ከቀጠለ አገራቸውን ያጠፏታል። እመነኝ! አንዳቸውም ተጠቃሚ አይሆኑም።”

አስተያየት አልሰጠሁም።ወዳጄ ጥያቄውን ቀጠለ፣

“አንዳርጋቸው ጽጌ በወያኔ ቴሌቪዠን የተናገረውን ሰማህ?”
“አልሰማሁም። ምን ተናገረ?”
ባጭሩ ጨምቆ ከነገረኝ በሁዋላ ከኔ አስተያየት ፈለገ፣
“በጠላቶቹ እጅ የወደቀ ሰው በሚናገረው ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጥም።” ስል ዘጋሁት።
“በርግጥ አንዳርጋቸው በጠላት እጅ ላይ ወድቆአል ብለህ ታምናለህ?” ሲል አክርሮ ጠየቀኝ።
“ሌላ መረጃ እስከሌለኝ ድረስ የማምነው እሱን ነው።”

ግንቦት 7፣ ኪሩቤል በቀለና ግርማ ካሳ ከአንዳርጋቸው ጋር በተያያዘ ያስነበቡን ፅሁፍና መግለጫ ግን ተስማምቶኛል። ግንቦት 7 “ሁላችንም አንዳርጋቸው ነን” የሚል ቀዳሚ መፈክሩን፣ “አንዳርጋቸውን እንሁን!” ወደሚል ማስተካከሉ ልክ ነው። “ነን” ለማለት ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል። “እንሁን” ግን ጥሪ ነው።ኪሩቤል ያመነበትን በስሙ ለመፃፍ አንጀት ያለው ሰው መሆኑ ይታወቃል። የአንዳርጋቸው ደጋፊዎች ተግባር እንደሚያንሳቸው መረር ባለ ብእር ፅፎአል። ግርማ ካሳ የአንዳርጋቸው ንግግሮች ተቆራርጠው መቀጠላቸውን ጠቁሞናል። ፅሁፎቹ ሚዛናዊና አሳማኝ ነበሩ።

ወዳጄ፣ “ሁለቱ ድርጅቶች መዋሃዳቸው ለውጥ የሚያመጣ ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀኝ።
“አላውቅም።” ስል መለስኩ። “...የኦሮሞ ህዝብ በውህደቱ ቢካፈል ኖሮ በርግጥ አጀንዳው ይለወጥ ነበር። ያም ሆኖ የአንድነት ሃይሎች በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል ወያኔን ለማስወገድ የሚያደርጉትን ትግል ከልቤ እደግፋለሁ። ይህም ኦሮምያና ደቡብ ህዝቦችን መልሶ የማፈን አዝማሚያ እስከሌላቸው ድረስ ማለት ነው።” አልኩ።

በርግጥ ግንቦት 7 በፕሮፓጋንዳው የተሳካ ስራ ሲሰራ መቆየቱ የሚታመን ነው። አርበኞች ግንባር በፕሮፓጋንዳው ስራ ደካማ ቢሆኑም መሬት ላይ ከግንቦት 7 የተሻሉ ሆነው ቆይተዋል። የሁለቱ መዋሃድ ሁለቱም ያለባቸውን ደካማ ጎን ይሸፍንላቸዋል። በዚያም ተባለ በዚህ ወያኔ በተዳከመበት በዚህ ወቅት፣ አንዳርጋቸው ከተያዘ በሁዋላ ሁለቱ ድርጅቶች የተሳካ ውህደት ማድረጋቸው ለወያኔ መጥፎ ዜና ነው።

ዋጋው “30 ሚሊዮን ዶላር” የሚገመት ሄሊኮፕተር ኤርትራ ካረፈ በሁዋላ ወያኔ ተቸግሮ ሰንብቶአል። ወያኔ በቅድሚያ ያደረገው የአየር ሃይል አባላትን ሰብስቦ ማስፈራራት ነበር። የወያኔ ካድሬዎች፣ “እኛ እዚህ ደረስነው በአየር ሃይል አይደለም።” ብለው መፎከራቸውን ሰማን። ፎክረው ሳይጨርሱ  እንደገና አራት ፓይለቶች ኬንያ ገቡ። በዚህ ጊዜ ግን ወያኔ መደናበርና መንቀጥቀጥ ውስጥ ገባ። ፉከራቸውን ትተውና ረስተው፣ “ጥፋታችን ምንድነው?” የሚል መጠይቅ የያዘ ፎርም ለአየር ሃይል አባላት አሰራጩ። ከ23 አመታት በሁዋላ ጥፋታቸውን ለማወቅ መፈለጋቸው የሚያስቅ ነው። ጥፋታቸውን ለማወቅ ፎርም መነስነስ አስፈላጊ አልነበረም። በአየር ሃይል ብቻ ሳይሆን በመላ ሰራዊቱ ሹመት በዘር ላይ የተመሰረተ ነው። ከአንድ ብሄር አባላት በቀር ሌላው አይታመንም። እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይታያል። የወያኔ አየር ሃይል ምን አይነት ተቋም እንደሆነ ለማወቅ የተሾመ ተንኮሉን ፅሁፍ ማንበብ በቂ ነው። ግንቦት 7 እና ተሾመ ተንኮሉ በዚህ የአየር ሃይል መታመስና መተራመስ ውስጥ እጃቸው ካለበት፣ “እንኳን ደሳላችሁ!” እላቸዋለሁ።

የወያኔ ባለስልጣናት ከፍተኛ ሃብት በማጋበስ ስራ ላይ በመጠመዳቸው አገሪቱን በአግባቡ ለመምራት ጊዜ አጥተዋል። ልጆቻቸው እድሜያቸው ለስራና ለጋብቻ በመድረሱ ወጪያቸው በዝቶአል። ደረጃቸውን ከፍ በማድረጋቸው ብዙ ይፈልጋሉ። እናም ርግጥ ነው፤ ሺዎች የገበሬ ልጆች ህይወታቸውን የከፈሉለት ትግል የጥቂት ቡድኖች መጠቀሚያ ሆኖ ቀልጦ ቀርቶአል። ጥቂት የተደራጀ ሃይል ሊገለብጣቸው እንደሚችል በማወቃቸው ደግሞ ውስጣዊ ፍርሃታቸው ገደብ አልባ ሆኖባቸዋል።  

1 comment:

daniel said...

I just recently get know who you are, tho I disagree with most of your writings but I like your style, I enjoy your good work and thank you